
እዚህ ከቀያችን ፤ ሰርክ ተባራሪ
ባዕድ ተገፍታሪ ፤ ተሳዳጅ ደንባሪ
የትም የሚደፋ ፤ ወኅኒ ተወርዋሪ
መፈናፈን ባንችል ፤ በግፍ ብንቀጣ
ሠርተን መብላት ባንችል ፤ አማራጭ ብናጣ
መኖር ብንነፈግ ፤ ለመኖር ብንወጣ
በሞት ላይ አፍጥጠን ፤ ተመምን በፍርጠጣ
እግር ወደ መራን ፤ ወደ ሆነን ዕጣ፡፡
በስደቱም ምድር ፤ ከሰሜን ደቡቡ
በአራቱም አቅጣጫ ፤ በምሥራቅ ምዕራቡ
ግማሹ ተበልቶ ፤ በበረሀው አውሬ
በባሕሩ ዓሣ ፤ ሐዘኑ መረሬ
በሞት ጥላ አልፎ ፤ በገባበት ሀገር
ሌላ ዙር መከራ ፤ ደሞ ሌላ አሳር
ከፎቅ ተወርዋሪ ፤ መንገድ ተጣይ ደሀ
ተቀቃይ ተጠባሽ ፤ በእሳት በፍል ውኃ
ሠርተህ በላህ ተብሎ ፤ ለቁራሽ እንጀራ
እንደ ቅርጫ ሥጋ ፤ ቅመስ በገጀራ
በቤንዚን ተቃጣይ ፤ ላይገኝ እሬሳ
በውለታ ቢስ ትውልድ ፤ በሚያንስ ከእንስሳ
ይሄ አነሰንና ፤ አሁን በመጨረሻ
ክርስቲያን ስለሆን ፤ የክርስቶስ ድርሻ
ለዘለዓለም ሕይዎት ፤ ለአሳር መካሻ
በአረመኔ አራዊት ፤ በውለታ ቢስ ውሻ
የሰው ሥጋ ለብሰው ፤ በመጡ ሰይጣናት
በቡኤልዜቡል ልጆች ፤ በውሉደ አጋንንት
የሰው ልጅ ደም ብቻ ፤ በሆነ ጥማቸው
በገሀነም ልጆች ፤ በእርኩሰት ክብራቸው
እንደ መሥዋዕት በግ ፤ ታራጅ በጅሐድ ካራ
በአረር ተደብዳቢ ፤ ለማተቡ አደራ
መንግሥት አልባ ወገን ፤ ሀገር አልባ ዜጋ
ከቶ ወዴት እንሸሽ ፤ ወዴት እንጠጋ
የሚያሳደንን ሞት ፤ እንግልት መከራ
የት ሔደን እናምልጥ ፤ ማንን እንጣራ
ካንተ በላይ አምላክ ፤ ካንተ ሌላ ጌታ
ከቶ ማን አለና ፤ አዳኝ መከታ
የት ነው ሀገራችን ፤ በሰላም ማደሪያ
በእፎይታ መኖሪያ ፤ በክብር መቀበሪያ
ቢኖረንማ ሀገር ፤ ማደሪያ መኖሪያ
እያልን የምንጠራት ፤ ውድ እናት ኢትዮጵያ
ባለቤቷ ሆነን ፤ የምንደክምላት
አይሆንም ሳንባል ፤ የምንገነባት
ምን ታዲያ አሰደደን ፤ ከቶ ምን አስወጣን?
በአራቱም አቅጣጫ ፤ በሞት ላይ አፍጥጠን?
ወገን ተሰደንም ፤ ከሆነ የማንተርፍ
እንዲህ ያለ ዋጋ ፤ በከንቱ ከምንረግፍ
የሀገርን ጠላት ፤ ያሰደደንን ጠንቅ
ጉሮሮውን አንቀን ፤ ይዘነው በመውደቅ
ትርፍ እናትርፍባት ፤ ዋጋ ይኑራት ነፍስ
ሀገር ነጻ ትውጣ ፤ ስማችን ይሁን ቅርስ
ሞት በኛ እንዲበቃ ፤ አሰቃቂው ስደት
ትውልድ ተጻ እንዲሆን ፤ እንዲኖር ደኅንነት፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ ጩሂ ፤ እሪ በይ እማማ
መጽናናት አትመኝ ፤ ልበሽ የሐዘን ሸማ
ከልዑል ማደሪያ ፤ ከሰማየ ራማ
እንደ ራሔል እንባ ፤ ለቅሶሽ እንኪሰማ
እንባሽ እስኪታበስ ፤ እስክትወጪ ከአድማ
ልጆቸን አስበሉ ፤ ታረዱ እንደ ኮርማ
አለቁብኝ በይው ፤ ቶሎ ፍረድ ፌማ፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሚያዝያ 12 2007ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment