
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያስታወቁት መጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕለት በዩኒቨርሲቲው የሴኔት አዳራሽ ለተለያዩ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች አጠቃላይ የመማር ማስተማርና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በተሰጠ መግለጫ ላይ ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲው በረዥም ዓመታት በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የሥራ ውሌ በሕገወጥ መንገድ ተቋርጧል›› በማለት ዩኒቨርሲቲውን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ‹‹መንግሥት ያወጣው የጡረታ መመርያ አለ፡፡ አንድ የአካዳሚክ ሠራተኛ የሚተካው ሰው ከሌለና የጡረታ ዕድሜው ከደረሰ ጡረታውን ማራዘም ይችላል፤›› በማለት የዶ/ሩ ጥያቄ ሕጉን ያልተከተለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ‹‹የአንድ ሠራተኛ የጡረታ ዕድሜ ለማራዘም መሥሪያ ቤቱ ፍላጎት ማሳየት አለበት፤›› ያሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ‹‹ሠራተኛው ይጠቅመኛል ወይ፤ የሚሠራው ሥራ አለ ወይ ብሎ ገምግሞ ማስታወቂያ መውጣት አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ሒደት አለው፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና የትምህርት ክፍላቸው እሳቸውን ለማቆየት ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁንና ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ኮንትራት መፈረማቸውን በድንገት ምክንያቱ ሳይገለጽላቸው የቅጥር ውላቸው መቋረጡ እንደተነገራቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የሥራ ባልደረባቸውና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑም በዚሁ ጉዳይ ደስተኛ ባለመሆናቸው ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የንግድ ተቋማትን ማቋቋሙን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተገልጿል፡፡ ‹‹የንግድ ተቋማትን በዚህ ዓመት አቋቁመናል ሥራ አስኪያጆችንም እንዲሁ መድበናል፡፡ እነዚህን የንግድ ተቋማት ስናቋቁም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በአጠቃላይ ራሳቸውን ችለው ገቢ የማመንጨት ሥራ እንዲሠሩ ነው፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ ገቢ እንዲያመነጩ ከተለዩት የዩኒቨርሲቲው ተቋሞች መካከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ማተሚያ ቤት፣ ቡክ ሴንተር፣ ደብረዘይት የሚገኘው የእንስሳት ማደለቢያ ይገኙበታል፡፡
No comments:
Post a Comment