Saturday, April 25, 2015

“እንደኔ አመለካከት ሰላም አንጻራዊ ቃል ነው” – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “እንደኔ አመለካከት ሰላም አንጻራዊ ቃል ነው” – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

“እንደኔ አመለካከት ሰላም አንጻራዊ ቃል ነው” –  ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋበቅርብ የሰማያዊ ፓርቲን ፕሮግራም ለመገምገም ተጋብዤ ግምገማዬን በጽሑፍ ካቀረብኩ በኋላ ከታዳሚዎቹ ውስጥ አንዱ ተነስቶ በቁጣ “በሀገሪቱ ሰላም አለ ብለሃል፣እኔ ግን አይመስለኝም ብሎ ዜጎች ከኢትዮጵያ እየተሰደዱ ነው “ በማለት ማሳያ አቀረበ፡፡
እኔ ስመልስለት አቀራረቤ በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አለ ወይንም የለም ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ሳይሆን የመንግስት ሹመኞች ሁልጊዜ እንደሚያቀርቡት በዚች ሀገር ሰላም ያለው ዴሞክራቲክ የሆነ ሥርዓትና የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ሕገ መንግሥት ስለተቀረፀ ነው ብለው የሚያቀርቡትን ለመተቸት የቀረበ ሐሳብ ነው፡፡
እንደኔ አመለካከት ሰላም አንጻራዊ ቃል ነው፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት አሁን የሌለው ሥርዓቱ እንደሚያወሩት ዴሞክራሲያዊ ስለሆነና የብሔር እኩልነት ስለተከበረ ሳይሆን በአንጻሩ መሳሪያውም ሆነ የሰራዊቱ ዕዝ በአንድ ክልልና ብሔር ተቆጣጣሪነት ስለወደቀ (Monopoly of Violence) ነው ፡፡ ይሄም ማለት የሀገሪቱ ሰላም በመሳሪያ እና በጉልበት የተያዘ በመሆኑ፣ ታሪክ እንደሚያሳየን በዴሞክራሲ ሳይሆን በወታደር ጥበቃ ላይ የተመረኮዘ ሰላም ዘለቄታ እንደማይኖረው ማንኛችንም እንረዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

እኔ እስከምረዳው ድረስ ሰዎች ከሀገራቸው የሚሰደዱት አንድም በጦርነትና በሰላም እጦት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከጭቆና ሥርዓት ለመሸሽ እንዲሁም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ገቢ ለማግኘት ይመስለኛል፡፡

ወደአዲስ ቲቪ በምንመጣበት ጊዜ ቃለ መጠይቁ የተካናወነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ስወጣ ለምነውኝ የሰጠሁት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ወቅቱ ደግሞ ISIS ሊቢያ ውስጥ አሰቃቂ ግድያ ከመፈጸሙ በፊት ነው፡፡

መቼም ለቴሌቪዥኑ ሰፋ ያለ ትችት ስለ ፀረ ሽብር ሕጉ፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሌለ፣ ሐሳብን በነጻነት የማቅረብ መብት እንደሌለ ወዘተ አቅርቤ ነበር፡፡ ሆኖም እንደተለመደው ቆራርጠውና መዝዘው ለእነሱ እንደሚመች አድርገው አቀረቡት፡፡

ከዚህ ተደራጅቶ ከሚዋሽ ቡድን ጋር ቀልቤ እያወቀው መነጋገሬ እኔን በእጅጉ ጥፋተኛ ያደርገኛል፡፡ምንአልባት የሰላም መኖርና አለመኖርን የጥያቄ ድባብ አንባቢያን ትረዳላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ላይ ISIS በተባለው ቡድን ሊቢያ ውስጥ የተፈጸመው አስከፊ ድርጊት እጅጉን አሳዝኖኛል፡፡ ተገቢ ባልሆነው የመንግስት ድርጊት ዙሪያ በቅርቡ ጽሑፍ አቀርባለሁ፡፡
ከፍ ካለ ምስጋና ጋር!

No comments:

Post a Comment