Friday, April 24, 2015

እናት ኢትዮጵያ አደይ ኤርትራ – ከአንተነህ መርዕድ እናት ኢትዮጵያ አደይ ኤርትራ – ከአንተነህ መርዕድ

እናት ኢትዮጵያ አደይ ኤርትራ – ከአንተነህ መርዕድመሳይ መኮንንና ፋሲል የኔዓለም ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ የብዙ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም የኤርትራውያን ወንድምና እህቶች ቀልብ መሳቡ እሙን ነው። በተለይም የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ መጠይቅ በብዙ መልኩ አስደምሞናል። እድላችን የተቆራኘነውና መነጋገሩና መብሰልሰሉ የሚገባ በመሆኑ ያለፍንበትን ሁሉ በትዝታ እንድፈትሽና አሁን የደረስንበትን እንዳይ ምክንያት ሆኖኛል። ነገሮችን ውስብስብና አጠቃላይ ከሆነ መልኩ ይልቅ ተጨባጭ ከሆኑ የግል ገጠመኞች ዙርያ ማውጋቱ የበለጠ ጉልህ ያደርገዋልና አንባቢዎቼም የራሳችሁ ገጠመኝ ዙርያ እየተሽከረከራችሁ የእኔን እንድትካፈሉ እጋብዛለሁ። በዚህ መልኩ ከምን ተነስተን የት እንዳለን ይታየናል።
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1966 ዓ ም ባህርዳር አፄ ሰርፀ ድንግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል አንድ ጠረጴዛ ተጋርቼ ከሁለት የኤርትራ ክፍለ ሃገር ተወላጆች ጋር ተቀምጫለሁ። በተለይ አንደኛው ባህርዳር ተወልዶ ያደገ የብቸኛው የከታማው ትልቁ ፋርማሲ ባለቤት የአቶ ማሞ ልጅ ነው። ሁለተኛው ጓደኛችን አስመራ ቢወለድም እድገቱ ባህርዳር ነው። አስራ አራቱንም ጠቅላይ ግዛቶች የያዘች የኢትዮጵያ ካርታ ሽፋን ያለበት ደብተር ሁላችንም ነበረንና የሁለታቸውም ደብተር ላይ የኤርትራን ካርታ በከለር አድምቀውበት “አደይ ኤርትራ” እያሉ እኔ ጓደኛቸውም እንዳይ እያደረጉ ወደ ልባቸው እያስጠጉ ያቅፉና ካርታውን ይስማሉ። ባግራሞት ስመለከታቸው ይውጣልህ ብለው ይመስላል “የአንተ አገር የቱ ነው?” ብለው ጠየቁኝ። ሙሉ የኢትዮጵያ ካርታን ሳመለክታቸው እየሳቁ “ኖ ኖ ኖ የተወለድህበትን ነው የምንጠይቅህ” አሉ፤ ከአካባቢው የመጣሁ የድሃ ገበሬ ልጅ መሆኔ ባይጠፋቸውም።
ባህርዳር ዕድሏ ሆኖ እንደሆነ አላውቅም ሰሞኑን ጎብኝቷት የመጣ ጓደኛዬ እንዳወጋኝ ከሆነ አሁን ደግሞ ትልልቆቹ ተቋማት ወዲህ ማዶ ባሉ ትግሬዎች ተይዘዋል። አንድ ውድ የግል ሆስፒታል ሊታከም ሄዶም ከተደረደሩት ተስተናጋጆች ሲቀላቀል ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ትግርኛ ሲነገር ሰምቶ ትግራይ ያለ ያህል ተሰምቶትም ተመልሷል። የድሮዋ ባህርዳር ሁለተኛዋ አስመራ ትባል ነበር። በውበቷ ብቻ ሳይሆን በነዋሪዎቿም ጭምር እንጂ (የዛሬዋን ሁለተኛዋ መቀሌ ብለዋት ከሆነ አላውቅም)። ትልልቅ የኤኮኖሚ ተቋማት ባብዛኛው የተያዙት በኤርትራውያን ነበርና። በሌሎች ከተሞችም ጉልህ ቦታ ቢኖራቸውም የባህርዳሩ ሚዛን ከሌላው ጋር ሲነፃፀር ከፍ ይል ነበር። ጋራጆች፣ ሱቆች፣ ዳቦቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ዳንስቤቶች፣ የቢስኪሌት መሸጫና መጠገኛዎች፣ ዘይት መጭመቂያዎች ወዘተ. ሙሉ በሙሉ እስከሚባል ድረስ በኤርትራውያን ከመያዛቸውም በላይ በጥጥ ፋብሪካው፣ በመዘጋጃ ቤቱና በልዩ ልዩ መስሪያ ቤት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸውና ትግርኛ ከአማርኛ ቀጥሎ የሚነገር በመሆኑ እኔም በሚገባ መነጋገር ጅምሬ ነበር። የምኖረው ኤርትራዊ በሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ ዶርም፣ የምመገበው እንደሁሉም የገጠር ልጆች አባ ነፀረ ቤት ልጆቻቸው መብራትና ተከስተ እያስተናገዱን፣ ብርሃነ፣ ጸጋ ዘአብ፣ ገብረሚካኤል( ኳስ ተጫዋቹ ጋራንቻ፣ ሻዕብያ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ሰምቻለሁ)፣ ሃለፎም በሚባሉ መምህራን እየተማርሁ፣ ኦሜድላ ሻይ ቤት የበረከተአብና ሌሎችን ኤርትራውያን ሙዚቀኞች ዜማ እያዳመጥሁ፣ ሲርበኝ እነአባ አድጎ ዳቦ ቤት አሶድ(ጥቁር ርካሽ የስንዴ ዳቦ) እየገመጥሁ በትግርኛ ሳወራርደው ኖሬ ቋንቋውን ብሰማው የሚደንቅ አይሆንም። በትልልቆቹ የኤርትራውያን ሰርግ ከአስመራ የሚያስመጡአቸው አዝማሪዎች ዘፈን ውበት አሁን ድረስ በትዝታ አዕምሮዬ ውስጥ ይንቆረቆራል። በህይወት ያሉ በርካታ ኤርትራውያን ያለዚያም ልጆቻቸው ያንን ያለፈ ጊዜ  እያስታወሱ እንደኔ እንደሚያዝኑ አልጠራጠርም። መሳይ “ኤርትራ ሄጄ ያጣሁዋትን ኤትዮጵያን አየሁዋት” ያለው በዚያ ወቅት መሃል አገር የነበሩትን ኤርትራውያንንና ልጆቻቸውን አይቶ ይሆናል። ያንን ስሜት የሻዕብያ፣ የደርግ ካድሬዎች ሆነ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ሊያጠፋው እንዳልቻለ እነመሳይ ታዝበዋል። ሁሉም ያልፋሉ። አገርና ታሪክ ይቀራሉ። ታሪክን አዛብተን እንድናይ ብዙ የደክሙ ያሰቡት ሙሉ በሙሉ የተሳካላቸው አይመስልም። እውነተኛ ታሪክ ሆነ የህዝብ ውስጣዊ ስሜት የሚዛቡ አይደሉምና።
በ1967 ዓ ም በአንድ ሌሊት ከደጀን እስከ ባህርዳር ባሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ኤርትራውያን መምህራን (እኔ የማውቀውን ማለቴ ነው። በመላ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ እንደነበር እገምታለሁ) ሻዕብያን ለመቀላቀል መሄዳቸውን ስሰማ እንደ አብዛኞቹ ጓደኞቼ ደነገጥሁ። አምና ሁለቱ ጓደኞቼ “አደይ ኤርትራ” ሲሉኝ ያልተሰማኝ እውነት አጥንቴ ድረስ ዘልቆ የዚያኔ ተሰማኝ። ፍሬወይኒ፣ ሉላን፣ ሃይሌን በትርፍ ጊዜዬ ስለማስተምራቸው ዶርሙን ከነጓደኞቼ የሰጡኝ አቶ አሰፋ አብርሃ ከአባት ያልተናነሰ ነበር የሚረዱን። ጥጥ ፋብሪካ ውስጥ ከፍተኛ መካኒክ ናቸው። ከፋብሪካው ቀጥ ብለው ወጥተው ባህርዳር ጋራጅ የሚባለውን ትልቅ ንብረታቸው ውስጥና የፍራሽና የቀለም ሱቆቻቸው ሲሠሩና ሲቆጣጠሩ ውለው አምስት ሰዓት የማትሞላ ጋድም ለማለት ቤታቸው ሲመጡ በጥናት ላይ ያለነውን አበረታትተውን የሻይ መጠጫ ለግሰውን ይሄዳሉ። አንድ የጭነት መኪና ከነተሳቢው ነበራቸው። እኒህ ቢሠሩ የማይደክማቸው ጥሩ ሰው ብርሃኔና ሃይሌ የሚባሉ ወንድ ልጆቻቸውን ከእሳቱ ለማሸሽ በሱዳን በኩል ውጭ አገር ከላኩ በኋላ ሴት ልጆቻቸውንና ንብረታቸውን ይዘው እንደ መምህራኖቼ ወደ “አደይ ኤርትራ” ሄዱ። ምን ያህል እንደተሳካላቸው ዛሬ አስመራን ያየ ይገምተዋል። በመሳይ መኮንንና በፋሲል የኔዓለም ዐይን አስመራን ስፈትሽ አቶ አሰፋን፣ ቢስኪሌት ጠጋኙን አስመላሽን፣ ያስተማርሁዋቸውን እነፍሬወይኒን፣ አስተማሪዎቼንና ተማሪ ጓደኞቼን ነበር ባስመራ ጎዳናዎች የምፈልገው። “ህልማችሁ እውን ሆነን?” እያልሁ እጠይቃለሁ። ካሉ ያለፈ ህይወታቸውን በትዝታ እንደኔ እየኖሩ እንደሆኑና ያንን የትዝታ ዘመን እንዲመለስ ሁል ጊዜ እንደሚያልሙ አልጠራጠርም።
“አደየ ኤርትራ” ነፃ እስክትወጣ ወደነበረው ሁኔታ አልመልሳችሁም። ያ ህልማቸው ወደትግል ተቀይሮ የብዙ ሺህ ወገኖቻችን ህይወትና ኑሮ ከሁለቱም በኩል ቀጥፎ ከበላ በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን ተጎናጽፋለች። ነፃነት መጎናጸፍ ብቻ ሳይሆን ሻዕብያ የኢትዮጵያም የኤርትራም ገዢ እስከመሆን የደረሰበት ጊዜ ነበረው። የኤርትራው አምባሳደር ሃይሌ መንቆርዮስ “ከጠቅላይ ሚኒስትር” ታምራት ላይኔ በላይ በኢትዮጵያ የሚያዙ፣ የሚናዝዙ እንደነበር እንዴት ይረሳል? ትልልቆቹ የህወሃት መኳንንት የሻዕብያ ሰዎች ባሉበት ቦታ ደረታቸውን ነፍተው መዝናናት እንደማይችሉና ድንክነት እንድሚሰማቸው አይተናል። ያ “የትንሽነት” ስነልቦና ወያኔና ሻዕብያ ለጫሩት ዳግም እልቂት አንዱና ዋናው ምክንያት እንደነበር የሚያከራክር አይደለም።
ሻዕብያዎች የተመኙትን ነፃነት ከፍተኛ መስዋዕት ከፍለው ከተጎናጸፉ በኋላ በኢትዮጵያውያን ኪሳራ የታላቋን ኤርትራ “አፍሪካዊት ማሌዥያ”  አዲስ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሁሉንም መንገድ ሲጠቀሙ (ልክ ዛሬ ወያኔ በሌላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ትግራይን አለማለሁ ብሎ እንድሚፍጨረጨረው)ቀሪው ኢትዮጵያዊ በአርምሞ እየተመለከተ ተቃውሞውንም እያሰማ ባለበት ጊዜ ህዝብን የሚቀጠቅጠው ወያኔ ነበር። በውጊያ ጊዜ ሆነ ከድል በኋላ የተዘረፈው የጦር መሳርያ የድል አድራጊነት ስካር ጋር ሲቀላቀል ቀልብ ይነሳልና ሁሉንም ጎረቤቶቻቸውን ሻዕብያዎች መጎሻሸም ጀመሩ። በድል ማግስት የመንን በሃኒሽ ደሴት ለመውረር ፉከራው ሲደምቅ የኢትዮጵያን ሰራዊትና መሳርያም ለመጠቀም መብቱ ነበራቸው። በአገሪቱ ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ ትልቁ ባለስልጣን የኤርትራው አምባሳደር ሃይሌ መንቆርዮስ ነበሩና ቢሮአቸው ጠርተውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡን ብዙ ፍሬ ከርስኪ ነገር አዳምጠን አንድ ያላሰቡት ጥያቄ ወረወርንላቸው። “አሁን የመን ጋር በሃኒሽ ደሴት ምክንያት ጦርነት ልትገቡ መሆኑን ሰምተንዎታል። ኢትዮጵያ ጋር የጋራ የመከላከያ ውል አላችሁና በውሉ መሰረት በአሁኑ ጦርነታችሁ ኢትዮጵያ ትረዳችኋለች?” የሚል ፈታኝ ጥያቄ። አዎን ማለትም ሆነ አይሆንም ማለትም የራሱ ጉዳት አለውና አንገታቸውን ደፍተው ብዙ አሰቡ። ፀጥታ ነገሰ፤ ቀና አሉና “ በስምምነታችን መሰረት ኢትዮጵያ ኤርትራን የመርዳት ግዴታ አለባት” ብለው በረጂሙ ተነፈሱ። ለእኛም ትልቁ ዜና ይህ ነበርና በግል ጋዜጦች፣ በቪኦኤ፣ ሮይተርስ ተሰራጨ። ድብቁ ስራቸው ባላሰቡት መንገድ አደባባይ መውጣቱ በህወሃትና በሻዕብያ ሰፈር እንቅልፍ የሚነሳ ውዝግብ ፈጠረ። ጦርነቱም ተካሄደ፤ ከኢትዮጵያ የተጫነ መሳርያ ሚሳይል ሳይቀር ጥቅም ላይ ዋለ። ወያኔና ሻዕብያ ጫጉላ ላይ ስለነበሩ ቤትህ ቤቴ፣ ንብረትህ ንብረቴ ሲባባሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ተመልካች ነበር። ለሃኒሽ የተዋሱት መሳርያም በዚያው ቀረና ኋላ ላይ ባደረጉት ጦርነት ኢትዮጵያውያንን ለመጨፍጨፍ ጥቅም ላይ ዋለ።
ባህርዳር ላይ ያመላከትኋችሁ የሃይለስላሴ ጊዜ የኤኮኖሚ ተሳትፎ በፖለቲካው ታግዞ ከኤርትራ ነፃነት በኋላ መላ አገሪቷ ላይ የኤርትራውያን እንቅስቃሴ ወደ ግልፅ ዘረፋ ተሸጋገረ(ልክ ዛሬ ወያኔና የጥቅም ተካፋዮቻቸው ውስን ትግራዋዮች እንደሚያደርጉት ማለት ነው) ። የኤርትራ ነጋዴዎችና መንግስት ቀረጥ ያልተከፈለበት ሸቀጥ በመላ አገሪቷ በማራገፍ ሌሎችን ኢትዮጵያውያን ከስራ ውጭ ሲያደርጉ ኤርትራ ከመሬት ተነስታ ቡናና አጣና ለዓልም ገበያ አቅራቢ ሆነች። የዛኔ የዘረፋ ስልቱን በሚገባ ያልተካኑት ወያኔዎች ለሻዕብያዎች ድጋፍ እየሰጡ ለዛሬ የሚጠቅማቸውን ልምድ እየቀሰሙ ነበር። በጊዜው ዜና አገልግሎት እሰራ ነበርና በምንፈልገው ርዕስ ጥናታዊ ዘገባ እንድናቀርብ ስንታዘዝ የቡናን ጉዳይ መረጥሁና በርካታ ቡና ላኪ ኢትዮጵያውያንን ኢንተርቪው በማድረግ አሰብና ምፅዋ ወደብ ቡናቸው እንዴት እንደሚዘረፍ፣ በሥራቸውም ላይ ያስከተለውንለውን  አደጋ፣ ኤርትራም አንድ እግር ቡና ሳታበቅል ቡና ላኪ መሆኗን የሚገልፅ ሪፖርት አቀረብሁ። ብዙ የመቆራረጥ ስራ በአለቆቼ ተሰርቶበትም ዜናው ሲለቀቅ አገር አነቃነቀና የዛሬ ሪፖርተር ባላቤት ወያኔው አማረ አረጋዊ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ቁልፍ ቦታ ነበረውና እንዳይሰራጭ  ለማድረግ ሞከረ። ነገር ግን አንዴ ከተለቀቀ በኋላ የግል ጋዜጦች ተቀባብለው ስላሸራጩት እኔም ለብዙ ግምገማ፣ ኢንተርቪውን የሰጡት ቡና ላኪዎችም የሻዕብያና የወያኔ ጉሸማ ደርሶባቸዋል።
ከሻዕብያዎች ዘረፋ በቂ ልምድ ያካበቱት ወያኔዎች የበይ ተመልካች መሆኑ አልተመቻቸውም። ዛሬ እነ አቶ ገብሩ አስራት፣ እነስዬ አብርሃ እንደሚተርኩት በሁለቱ አገሮች መካከል የተለኮሰው ጦርነት የሉዓላዊነት ወይንም የወደብ ጉዳይ አልነበረም። የዘረፋው ሙሉ ተጠቃሚ ወያኔና ደጋፊዎቹ ብቻ እንዲሆኑ ሻዕብያና ሌሎቹ ኤርትራውያን የያዙትን ተቋምና ጥቅም ሙሉ በሙሉ አስለቅቆ መቆጣጠር ነበር አላማቸው። ያ ለመሆኑ የነአቶ ገብሩ ኑዛዜ ሳይሆን አሁን በተጨባጭ ያለው እውነታ አጉልቶ ይመሰክረዋል። (የገብሩ አስራት ኑዛዜ ያልሁበት ምክንያት አለኝ። ኑዛዜና ንስሃ ልዩነት አለው። ንስሃ ካለፈ ሃጤአት ሙሉ በሙሉ ለመንፃት ከልብ የሚደረግ ሲሆን፤ ኑዛዜ ሲሞቱ፣ ሃቅም ሲያጡ የግብር ይውጣ ልፍለፋ ነው። ቱባ ወያኔዎቹ ቀን ከጣላቸው በኋላ ንስሃ አልገቡም። በዚህ አጋጣሚ አቶ ገብሩ የጻፉት መጽሃፍ አንዳንድ መሰረታዊ እውነቶችን ሆን ብሎ የሳተ ከመሆኑ ውጭ ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ተነቅሰው የሚወጡለትና መነበብ ያለበት መጽሃፍ በመሆኑ ስራቸውን አደንቀዋለሁ። ሳላምሰግናቸውም አላልፍም። )
መሰረታዊው የወያኔና የሻዕብያ ጠብ የጥቅምና እሱን ማስጠበቅ የሚያስችለው የፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና ነው። በተረዳዳ የፍጥኝ አስረው የጣሏትን አገር ተስማምተው ለመዝረፍ ከልክ ያለፈ ስስታም ባህሪያቸው አልፈቀደላቸውም። “በሚስቴ ውሽሞቿ ተጣልተው ገላጋይ ሆኜ አመሸሁ” እንዳለው ፈሪ ሆነን እኛም አንድ ጊዜ አንዳቸውን ሌላ ጊዜ ሌላቸውን በማሞገስና በመንቀፍ ያላዋቂ ሙያ ላይ ተጠምደን በመገኘታችን አሳዛኝ ሁኔታ ላይ አገሪቱን በመጣል የተወሰነ ድርሻ አለን።
ኢሳያስን አገር ወዳድ ኤርትራዊ፤ ወያኔንም የትግራይ ህዝብ ጠበቃ አድርጎ ማየት ቢያንስ የዋህነት ሲበዛ ደግሞ የፖለቲካ መሃይምነት ነው። ለማንኛውም አምባገነን ሁሉንም ሊያስገኝለት የሚችለውን የፖለቲካ ስልጣን ሊያስጠብቅለት እስካልቻለ ድረስ አገርና የተወለዱበት ቦታ ትርጉም የለውም። ብዙዎቻችን በጅልነት፤ ብልጦች ደግሞ ለፖለቲካ አላማ እንደፋሺን የምንጨማለቅበትን የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጠንሳሹ  እ ኤ አ 1878 ጆርጂያ ጎሪ የሚባል ቦታ የተወለደው ስታሊን የጠቅላላው ሩስያ መሪ ከሆነ በኋላ ዘመዶቹ ጆርጂያዎች የመብት ጥያቄ ሲያነሱ በብረት ክንዱ ነው የደፈጠጣቸው። የኦስትርያ ተወላጁ አዶልፍ ሂትለርስ ጀርመንን ሲመራና ዓለምን ለመዋጥ ሲያዛጋ መጀመርያ ቁርስ ያደረጋት ኦስትርያን አይደል? ኢሳያስንና መለስን በኤርትራዊነት፣ በትግራዋይነት፣ ወይም  በኢትዮጵያዊነት መፈረጅ ከንቱ የሚሆንበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሁለቱም የሚሉትን አይደሉምና። ለአምባገነኖች አገር ግላዊ ጥቅም፣ ክብር፣ ዝናና ስልጣን ነው። አገር እውነተኛ አገር የሚሆነው ለተራው ህዝብ ብቻ ነው።
ሰሞኑን በፌስ ቡክ ያገኘሁት የኢሳያስ አፈውርቂ ሃረግ ይህንን እውነት ያረጋግጥልኛል። እውነትነቱ መጣራት ስላለበት እንዳለ አቀርበዋለሁ። የምታዳብሩም ሆነ የምትሞግቱት ካላችሁ ቀጥሉበት። መሰረታዊ እውነቱ ላይ ግን ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም። እንዲህ ቀርቧል፤
ኢሳይስ አፈወርቂ
———————-
ኢሳይስ አፈወርቂ በአሁኑ ሰዓት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቅ ለረጅም አመታት ለኤርትራ ነፃነት የታገሉ መሪ ናቸው። የኢሳያስ አፈወርቂ አባት አቶ አፈወርቅ አብርሃ ይባላሉ፤ እናታቸው ወይዘሮ አዳነች በርሄ ይባላሉ።
ልጆቻቸዉም፦
አቶ አማረ አፈወርቅ (አፈወርቂ)
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ
አቶ አማኑኤል አፈወርቅ
አቶ ኤርሚያስ አፈወርቅ
አቶ ዮናስ አፈወርቅ
ወ/ሮ ጽጌረዳ አፈወርቅ
ወ/ሮ አርዮን አፈወርቅ ናቸው።
የኢሳያስ አባት አቶ አፈወርቅ የመጡት ከትግራይ ተምቤን ሲሆን ዘራቸዉ የኢትዮጵያ አካል ከሆነዉ ከአጋሜ አዉራጃ የተዉጣጣ ነዉ። የአቶ ኢሳያስ አባት ይሰሩ የነበሩት በትግራይ አስተዳደር ክፍለ ሃገር በመቀሌ መዲና ነበር። ጡሮታ እስከወጡም ድረስ በመሬት ንብረት ይዞታ ማሻሻያ ሚኒስቴር ዉስጥ ነበር የሚሰሩት። ጥቁር ሙሉ ልብስና ጥቁር ክራባት ለባሽ ተብለዉ ይጠሩ እንደነበር ይነገራል። («ካንትሪ ጀንትል ማን» ተብሎ አንዳንዴ ከሚታወቀዉ ከጥቁር ሱፍ የተሰራ ክብ ቆብ ከራሳቸዉ አይለዩም ነበር።) ጋዜጣም ከእጃቸዉ በፍጹም አይለዩም ነበር።
በናታቸዉ በኩል የኢሳያስ አጎቶች፦
ደጃዝማች ሰለሞን አብርሃ
ካፒቴን መኮንን አብርሃ
አቶ ሓጎስ አብርሃ ናቸዉ።
የአቶ ኢሳያስ አጎት ደጃዝማች ሰለሞን አብራሃ (በጊዜዉ ሲጠርዋቸዉ በነበሩ ጋዜጦች አጠራር «ሰለሞን አብሃም») በዓጼ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት ማለት (በ1946 ዓ.ም.) የወሎ እንደራሴ ሆነዉ ያገለገሉ ናቸዉ። በዚያ ጊዜ መቀሌ ከተማ ዉስጥ ተደራጅቶ የነበረዉ የባህል ቡድን አስመራን ከጎበኘ በሗላ ወደ ደሴ መጣ። እንደራሴዉ ደጃዝማች ሰለሞን ለክብር እንግዶቹ በተዘጋጀዉ የእራት ግብዣ ላይ ምስጋናቸዉን ለቡድኑ ከገለጹ በሗላ እሳቸዉም ትግሬ መሆናቸዉን አንስተዉ የባህል ቡድኑ የትግራይ ባህላዊ ሙዚቃ እና ባህላዊ ዉዝዋዜ ለማስፋፋት ላደረገዉ አስተዋጽኦ አድናቆታቸዉ ገለጹ።
በተጨማሪም የደጃዝማች ሰለሞን እናትም አጋሜ አዉራጃ ዉስጥ ተወላጅ ትግሬ መሆናቸዉን እና አባታቸዉም በትግራይ ክ/ሃገር ዉስጥ የተምቤን ተወላጅ መሆናቸዉን አንስተዉ ለባህል ቡድኑ ገልጸዉላቸዋል።
የባሕር ሃይል ካፒቴን የሆኑት ካፒቴን መኮንን አብርሃ የእቴጌ መነን ትምሕርት ቤት ተማሪ የነበረቺዉ የደጃዝማች ገብራይ ልጅን አግብተዉ ሦስት ልጆች እንደወለዱ ይታወቃል። አቶ ሐጎስ አብርሃም ቢሆን በአዲስ አበባ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የጥንት ተማሪ ሲሆን ለዚያዉ ተማሪ ቤት የእግር ኳስ ቡድን በረኛ ነበር፣ ሆኖም በበሽታ ምክንያት ትምህርቱን አቋርጦ ለጥቂት ጊዜ በብሔራዊ ባንክ ስራ ተቀጥሮ እየሰራ እንዳለ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየ ይታወቃል።
የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አያቶችና ሌሎች ዘመዶቻቸዉም – በሚመለከት፦ በእናቱ በኩል የኢሳያስ አፈወርቂ አያት (የእናት እናት) ወይዘሮ መድህን «በራድ» ይባላሉ። በራድ (ተብለዉ በቅጥያ ስም የተጠሩበት ምክንያት ወ/ሮ መደህን በጠጅ ስራ ንግድ ተሰማርተዉ ይኖሩ ስለነበር «ጠጅ» ባካባቢዉ የሚቀዳዉ «በራድ» ተብሎ በሚታወቀዉ «ማንቆርቆርያ» ስለነበር ነዉ። መድህን የኢሳያስ እናት የወይዘሮ አዳነች በርሄ እናት ናቸዉ። ኢሳያስ የልጅነት ትምህርቱን የተከታተለዉ በሴት አያቱ በወይዘሮ መድህን ተንከባካቢነት ነዉ። ወ/ሮ መድህንም በትዉልዳቸዉ ዓድዋ ሲሆኑ፣ የፊታዉራሪ ኪዳነ መስቀል አጎት ናቸዉ።
ፊታዉራሪ ኪዳነ የአቶ የማነ ኪዳነ (የየማነ ጃማይካ) አባት ናቸዉ ይባላል። ይህ እዉነት ከሆነ የአቶ የማነ ኪዳነ (ጃማይካ) እና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ «በኢትዮጵያ አጠራር» ወንድማማቾች ናቸዉ። በአዉሮጳዉያኖች አጠራር ግን «የአጎት ልጆች ናቸዉ»። ባጭሩ አሥመራ የሚገኙ አክራሪ ጠላቶች ናቸዉ የሚባሉት አብዛኛዎቹ የትግራይ ዝርያ የሆኑና በተለይ ከትግራይ በጠቅላላም ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የስጋ ፣ የአጥንት እና የደም ቁርኝት ያላቸዉ ናቸዉ። የኢሳያስ አክስት (የኢሳያስ እናት እህት) ወ/ሮ ሃና ይባላሉ። የአቶ በላይ ባለቤት ናቸዉ። አቶ በላይ የዓድዋ ሰዉ ናቸዉ። እንደሚባለዉም ልጆቻቸዉ ስዊድን ሃገር ዉስጥ ይኖራሉ። በእናታቸዉ በኩል የአቶ ኢሳያስ አጎት የሆኑት ከዓድዋ ተወላጅ ከሆኑት በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ዉስጥ የሚኖሩ ወ/ሮ ዘዉዴ የሚባሉትን ወልደዋል። ከላይ በተገኘዉ መረጃ መሰረት የአቶ ኢሳያስ ኤርትራዊነት ኤርትራ መሬት መወለዳቸዉ ብቻ ነዉ። የአቶ ኢሳያስ ባለቤትም ወ/ሮ ሳባ ሃይለ ይባላሉ። ኤርትራዊት ናቸዉ። (ምንም እርማት ሳላደርግ ነው ያቀረብሁት)
ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ እናታቸው ወይዘሮ አለማሽ ገብረልዑል ኤርትራዊ መሆናቸውና ለ”ናፅነት” ድምፅ መስጠታቸው ለብዙ ኢትዮጵያውያን ትርጉም ያለው ቢሆንም ለመለስ ምንም እንዳልሆነ አይተናል። ትልልቆቹ የወያኔ ባለስልጣናት  ከኢሳያስ የበለጠ የኤርትራ ዘር አላቸው። በስልጣን እስካቆያቸው ድረስ ኢትዮጵያዊ ነን ይላሉ፣ ያም ፈትና ላይ ሊጥላቸው ከሆነ ከሁሉ በፊት ትግሬ ነኝ ይላሉ። ጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ በአሁኑ ሰዓት የደቡብ ሱዳንን ኤኮኖሚ በመቦጥቦጥ ላይ ስላሉ ቢፈልጉ ከማቻር የበለጠ ደቡብ ሱዳናዊ ይሆናሉ። የወያኔ ትልቁ ችሎታና ባህሪ ደግሞ ይሄው ነው። እኛ ኢትዮጵያዊ ይመስሉን ይሆናል እንጂ በአንድ ሌሊት ሳውዲ አረብያዊ፣ ሱዳናዊ፣ ሶማሊያዊ፣ ቻይናዊ ሆኖ ማደርን የተካኑ ናቸው። ኢትዮጵያዊነትና ኤርትራዊነት ምናቸውም አይደለም።
የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ያንገበግበናል በማለት የሚያላዝኑ በስልጣን ላይ ያሉና ጡረተኛ ወያኔዎችን እውነተኛ ባህሪ   መመልከት ከሚናገሩት ሳይሆን ከተግባራቸው ነው። ዛሬ በተለያየ መልክ ስማቸውን የሚያጠፏቸው አፄ ሚኒልክ አድዋ ላይ በታሪካዊ ድላቸው ኢትዮጵያን ከወራሪ ነፃ ሲያወጡና ለዓለም ጥቁሮች ተምሳሌት ሲሆኑ በኋላቀር መሳርያ ተዋግተው የሞተባቸው የሰው ሃይል ከአምስት ሺህ አይበልጥም። ወያኔዎች የአስራ ሰባት አመት ጦርነት ልምድ ሻዕብያዎችም የሰላሳ ዓመት ልምድ አለን ቢሉም ከመቶ ዓመት በኋላ ባድሜን እንኳ ባላስለቀቀ ጦርነት ሰማንያ ሺህ ሰው ነው የሰውት። ባህር ተሻግሮ የመጣ ጠላትን በጎራዴ ያወራረዱ አባቶቻቸውን እረግመውና አውግዘው ከሰማንያ ሺህ በላይ ወንድሞቻቸውን ግድለው ነው ዐይናቸውን በጨው ታጥበው የሚፎክሩት። ከዚያ አልፈው መሬት ለሱዳን፣ ለቻይናና ለአረብ ሲያስረክቡ ያልታጠቀ ኢትዮጵያዊ እየገደሉ ነው። ይህንን የሚያይ እንዴት በኢትዮጵያዊነት ይመድባቸዋል።
የኤርትራ ደም ያላቸው ትልልቆቹ ወያኔዎች ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉ ኤርትራውያንን የዐይናችሁ ቀለም አላማረንም በማለት ንብረታቸውን ነጥቀው ሲያባርሩ ቅንጣት አልተሰማቸውም። ቀሪው ኢትዮጵያዊ ግን አልቅሶ እንደሸኛቸው የተባረሩት ኤርትራውያን ሁሉ የሚመሰክሩት ነው።
የሻዕብያና የወያኔ ፍቅር አልቆ ጠቡ በዜና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት የታወጀ እለት ማዕከላዊ እስር ቤት በአንድ ክፍል ውስጥ አስራ ሰባት ሰዎች ነበርን። እዚያች ክፍል ውስጥ የነበረው ድንጋጤ የመላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ ድንጋጤ ነበር። ከዜናው በኋላ የነበረውን የጥቂት ደቂቃ ፀጥታ መርፌ መሬት ላይ ብትወድቅ ታደፈርሰው ነበር። ሁሉም ራሱ ውስጥ ገብቶ እየመረመረ የአገሩን እድል ለማየት ይሞክር ነበር። እርግጠኛ ነኝ ያ የሃዘን ድባብ በሁለቱ ጦረኞች ባለስልጣናት ዘንድ አልነበረም። የጊዜውን የህወሃትን ትኩረት ለማወቅ የገብሩ አስራትን መፅሃፍ መመርመር ይበቃል። በዚያች ክፍል ሁለት ኤርትራውያን ነበሩ። ከነሱ ውጭ የድሮ ወታደር፣ ነጋዴ፣ በሙስና የተከሰሰ ሠራተኛ፣ ጋዜጠኛ፣ የፖለቲካ እስረኛ፣ በፎርጀሪ የታሰረ ሶማሌ ወዘተ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍልና ህብረተሰብ የተዘነቁበት ትንሿ ኢትዮጵያ ነበረች። ከትንሽ ፀጥታ በኋላ ውይይቱ ፈነዳ። ምንም ያልለየለት ጫጫታ፣ እርግማን፣ የታሪክ ትንተና፣ ፖለቲካዊ ትችት ባጠቃላይ መተኛት አልተቻለም። ያልታሰረውም ኢትዮጵያዊ የዚያን እለት እንዳልተኛ እገምታለሁ። ከሁለቱ ኤርትራውያን ጎይቶም የሚባለው የሻዕብያ የትዕቢት ሙሌቱን ትንሽ በመተንፈሱ ተተቸ እንጂ ወድያው ወደ ሰከነ ውይይትና መግባባት ነው የተሄደው። ህዝብ ይቻቻላልና። ሁለቱን ኤርትራውያን አንድም እንደጠላት የተመለከታቸው አልነበረም። ማዕከላዊ ውስጥ አማርኛ አቀላጥፎ የተማረውና “መንዜው” እያልን የምንጠራው ሶማሌያዊው ሊቨን ሳይቀር በውይይቱ ተሳትፏል።
ቆይቶ የኤርትራውያን ከአገር እንዲወጡ መወሰኑ ሲሰማ ሌላ ድንጋጤ ተፈጠረ። ሁላችንም አንገታችንን ደፋን። ሁለት ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንደሚባለው ሰለባው ህዝቡ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነበር። አንድ እሁድ ባለቤቴ ጋር መገናኘት ሲፈቀድልኝ ቀና ብላ ለማየት እንደፈራች ተገነዘብሁ። “ቤተሰብ ደህና ናቸው? ምን ሆነሻ?” የሚሉ ጥያቄዎችን አከታተልሁ። ደህና መሆናቸውን ነገረችኝ። “አበባ እንዴት ሆነች ይሆን በሰሞኑ ግርግር?” ስል ድንጋጤዋ ታየኝ። ፊቷ ቀድሞ መልሱን የነገረኝ ቢሆንም “ጭነው ከነልጆቿ አባረሯት” ስትለኝ ስሜቴን መቆጣጠሩ ተፈታተነኝ። አበባ ገብረእግዜብሄር ኤርትራ ተወልዳ አዲስ አበባ አድጋና ተምራ ለብዙ ዘመናት ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዜና አግልግሎት ሰርታ ለጡረታ የተቃረበች ትጉህ ሴት ናት። ከትምህርት ቤት ወጥተን ለተቀላቀልነው ስራውን ያስተማረችን ምስኪን የአራት ልጆች እናት አስተማሪዬም ጓደኛዬም ነበረች። ሰለሞን ገብረእግዜብሄር የተባለ የሬድዮ ጋዜጠኛ የመሃል አገር ሰው ባሏ በሌላ ክስ ታስሮ ብቻዋን ልጆቿን ስታሳድግ ኤርትራዊ ነሽ ተብላ በመጦርያ ዘመኗ ከነልጆቿ ባውቶቡስ ተጭና ድንበር ላይ ተወረወረች። ኤርትራን የት ታውቃታለች? በዚህስ እድሜ ምን ሰርታ ትኖራለች? ልጆቿስ የናታቸውን ወይም የአባታቸውን አገር የመምረጥ እድል አገኙ?  የግፉ ግፍ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ አንዱ ንግድ ስራ ኮሌጅ የጨረሰ ሌላ ሁለተኛ ደረጃ ያለ ወንድ ልጆቿን የጠበቃቸው ሳዋ ማሰልጠኛ ካምፕ ነው። ባላደጉባት ኤርትራ በኩል ተሰልፈው በግዴታ ታፍሰው ሆነ ተታልለው ከአዲስ አበባ የሄዱ በኢትዮጵያ በኩል የተሰለፉ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር እንዲጋደሉ ተደርገዋል። እነመሳይ አስመራን ሲያስሱ አበባና ልጆቿን በስሜት እቃኛለሁ። ከባህርዳር ተንስቼ እስከ አዲስ አበባ የግለሰቦችን ስም እያነሳሁ የዘረዘርሁት በተጨባጩ ከወዲህና ከወዲያ ያለውን ህዝብ እንድናይ ነው።
ፖለቲካ ስሜታዊ ያደርጋል። እውነቱ ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የተለየ ነው። በኢትየጵያ ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው በህዝቦች መካከል ያለው መቀራረብ፣ ዝምድናና ጥቅም በጥልቀት ሲታይ እንጂ ፕሮፓጋንዳ ሲያጠለሸው ፖለቲከኞችም ሲፏልሉበት አይደለም። የሰሞኑ ማዕበል ኢሳያስን በጭራቅነት ከመሳል መልአክ እስከማድረግ የዘለቀ ሆኗል። አሁንም እውነቱ ከሁለቱም አይደለም።
ኢሳያስ አፈወርቂ ከአምሳ አመት በላይ ያለተቀናቃኝ የሻዕብያን አመራር ይዘው ያሉ፣ ይቀናቀኑኛል ብለው ያሰቧቸውን ጓደኞቻቸውን የገደሉትን ገድለው ሌሎችን ከምድር በታች አስረው የሚያሰቃዩ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ላሰቡት ብሩህ ተስፋቸው የተሰውበትን ትግል ከራሳቸው ጭፍን ስልጣን አኳያ በማየት ወጣቱ በስደት ባህር ሲበላው፣ አካሉ ከነነፍሱ እየተቀደደ በአረቦች ሲሸጥ፣ አዛውንቶች ያለጧሪ ሲቀሩ ምንም የማይሰማቸው አምባገነን ሆነው እያለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስባሉ የሚል ካለ እሱ አላዋቂ ነው። ወይም ዋሾ ነው። በኤርትራ ህዝብ ስቃይ ላይ ከመዘባበት አልፎ በኢትዮጵያ እድል ላይም አዳጋ መጋበዝ ነው። በእርግጥ ኢሳያስ በሂደት የገቡበት አጣብቂኝ ብዙ ትምህርት ሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል። መለወጣቸው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አካሄድንና የፖለቲካ ነፃነትን እስከ መቀበል የዘለቀ እንዳልሆነ ግን በአገዛዛቸው መቀጠል እያስመሰከሩ ነው። ከዚያም በላይ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዲያብብ  ማገዙ ተመልሶ የራሳቸውን አምባገነናዊ ህልውና እንደሚፈታተን አጥርተው የሚያውቁ ብልጥ ፖለቲከኛ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ተባብሮ ለመስራትና ለመኖር የሚያስችሉ ብዙ እድሎችን ከዚህ በፊት አባክነዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ አክብረው በጋራ ጥቅም ዙርያ ቢሰሩ ኖሮ ዛሬ አንዲት ኩሬ ለመገደብ ቀኑን ሙሉ ደረቅ ደንጋይ ላይ ተቀምጠው ባልዋሉ ነበር። እነዚያ ታታሪ ኤርትራውያንም በመላ ኢትዮጵያ እንድልባቸው ተከባብረው ቢሰሩ ኖሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር አፍሪካዊት ማሌዥያ በሆነች ነበር። ዛሬ የሁለቱም አገር ወጣቶች የሜዲትራንያንና የቀይ ባህር አሳ ነባሪ ቀለብ፣ የአረብና የደቡብ አፍሪካ እንስሶች መጫወቻ ባልሆኑም ነበር። እሳቸውና አሁን ደመኛ ጠላታቸው ሆኖ የተቆጠረው ወያኔ በአጉል ስስት እዚህ አድርሰውናል። የሚያሳዝነው ሻዕብያ የሰራውን ተመሳሳይ ስህተት ወያኔ እየሄደበት መሆኑና ምስኪኑ የትግራይ ህዝብም ያለሃጢያቱ እንደ ኤርትራውያን ነገ መከራ ከፋይ እንዲሆን እየተገፋ መሆኑ ነው። ዛሬ ፀጥታን የመረጡ የትግራይ ልጆች ጊዜው ከዘገየ በኋላ ቢባንኑ ጥቅም የለውም።
ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ውድቀት፤ ወያኔዎችም ከመንግስቱ ውድቀት አልተማሩም። ይባስ ብሎ ወያኔዎች ከሻዕብያ ውድቀት አልተማሩም። አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንዲሉ ኢትዮጵያን እስከገዙ ድረስ ዘረፋውን ይቀጥሉበታል። ከስልጣን ከተወገዱም ትግራይን ይዘው ለመቀመጥ የእምቧይ ካብ እየካቡ ነው። ይህ ህልማቸው እውን የማይሆነው አንዱ ዋናው ምክንያት የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላታቸው ስለሚሆን ነው። በግድ ካደረጉትም አሁን የሻዕብያ መሪዎችና የኤርትራ ህዝብ ካሉበት የባሰ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው የታወቀ ነው። ለትግራይም ሆነ ለኤርትራ ህልውና መሰረት በከንቱ ብልጠት ያስቀየሙትና የአሰቃዩት ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ከመሃል ያለውን ስራቸውን ከበጠሱ እንዳያቀጠቅጡ ሆነው ይደርቃሉ። በሚገነቡት ሰማይ ጠቀስ ፎቅ አይኖሩበትም፣ በግፍ ያጋበሱትን ሁሉ ሃብት አይበሉትም፣ ያከማቹት ሁሉ መሳርያ አያድናቸውም፣ ያጀባቸው “ሆድና ኪስ አደር” እንደጥዋት ጤዛ ይበናል። ከህልማቸው ሲነቁ ራሳቸውን ከደደቢት ደንጋይ ላይ ተቀምጠው ያገኙታል። ከሃብት ጋር ያፈሩት የቅንጦት በሽታ ከቁጭትና ከእድሜ ጋር ተጋግዞ ወደ ባለ ራዕዩ መሪያቸው ይወስዳቸዋል።
የኤርትራም፣ የትግራይም ሆነ የቀሪው ኢትዮጵያ ህዝብ አምባገነን ግዥዎቹ እስካሁን የወሰዱትን የመከራ ዳርቻ ተገንዝቧልና በመቃብራቸው ላይ የጸና አገርን ይገነባል እንጂ አዲሱ ትውልድ በአሮጌ ጭራቅ ገዥዎቹ እየተጎተተ አይታረድም።
ይህንን ጽሁፍ በማጠናቀቅ ላይ እያለሁ ወንድሞቻችንን ደቡብ አፍሪካ በቁማቸው በእሳት ሲያቃጥሏቸው አይቼ ከድንጋጤ ሳልወጣ የሊብያውን እርድ ተመለከትሁ። አነባሁ። ስቃዩ እንዲሰማኝ ብዬ ራሴን ለመቅጣት ደጋግሜ አየሁት። ይመመኝ! ይመመኝ! ይመመን! ደጋግመን እንየው። አይሲስ አይደለም ያረዳቸው። እኛው እራሳችን ነን ያረድናቸው። እኛው ራሳቸን ያመጣነው፤ ተሸክመን ፣ችለን በፍርሃት የተቀበልነው ውርደት ነው። የገዛ ወንድሞቻችን ሲያርዱን ዝም ብለን የተቀመጥን ሙታን ነን። ከተደየንንበት፣ እንደሰጎን አንገታችንን ከቀበርንበት ሁላችንም ተነስተን እውነተኛ ድክመታችንን ካላየንና ካላረምን መፍትሄ የለንም። የባሰ ይጠብቀናል። ችግራችንን ከምንጩ ከማድረቅ ሌላ መፍትሄ የለም። በትክክለኛ አዕምሮ፣ በሰከነ ሁኔታ ላይ ስላይደለሁ ለጊዜው እዚህ ላቁም።
ኢትዮጵያን እንባዋን የሚያደርቁላት ልጆች ይስጣት! እኛ ልጆቿ ነን ለማለት የሞራል ብቃቱ የለንምና!

No comments:

Post a Comment