Monday, April 20, 2015

ቅ/ሲኖዶስ: በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ አወገዘ ቅ/ሲኖዶስ: በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ አወገዘ

ቅ/ሲኖዶስ: በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ አወገዘ

‹‹በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ኹሉ እናደርጋለን››

  • ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፤ አጥብቃም ታወግዘዋለች
  • ጭካኔው የማንኛውም ሃይማኖት ተቋም እና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር ነው
  • በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት አስፈላጊውን ኹሉ እናደርጋለን
  • ፓትርያርኩ የአርመን ክርስቲያኖች ዕልቂት ፻ኛ ዓመት ዝክር ጉዟቸውን ሰርዘዋል
  • የሦስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ይታወጃል፤ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል
በስመ አብ ወወልድ መወንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን፡፡
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ሀገር በንጹሐን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ አካባቢ አይ ኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ወገኖች ላይ አሠቃቂ ግድያ እንደተፈጸባቸው ዘግበዋል፡፡
በዘገባው፣ ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሐን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብአዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡
አሠቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን ወጣቶች ዜግነት እና ማንነት ግልጽ እና አስተማማኝ የኾነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢኾንም እስከ አኹን ድረስ በበርካታ የዓለም የዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው፣ የዚኽ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መኾናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ሓላፊነት በማይሰማቸው እና በእነርሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፤ አጥብቃም ታወግዘዋለች፡፡
ስለዚኽ፣ የዚኽ ግፍ ሰለባ የኾኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን፡-
  • በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ኹሉ የምናደርግ መኾኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ኹኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤
  • እንደዚኹም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መኾኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የኾኑ ኹሉ እንደ ቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚኽ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሳራ እንጂ ምንም ዓይነት ትርፍ የማያገኙ መኾናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment