Tuesday, April 28, 2015

የ“ቆንጆ” መፅሄት ባለቤት ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ አገር ጥሎ ተሰደደ

20887_443039482529535_42744021382446654_nላለፉት አራት ዓመታት ለንባብ ሲበቃ የቆየው የ“ቆንጆ” መፅሄት ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ አገር ጥሎ ተሰደደ፡፡ ጋዜጠኛው በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ደህንነቶች ቢሮው ድረስ በመሄድ ዛቻና ማስፈራራት ስላደረሱበትና ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ መገደዱን እንደነገራቸው ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የደህንነት ኃይሎች በየጊዜው ወደ ቢሮው እየሄዱ “ክስና እስር ይጠብቅሃል” እያሉ ያስፈራሩት እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፤ ፕሬሱን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እየተሰራ ስለመሆኑ፣ ዘጋቢ ፊልሙ ከሚሰራባቸው የህትመት ውጤቶች አንዱ “ቆንጆ” መጽሄት እንደሆነ መረጃ እንደደረሰውና ደህንነቶቹ በየጊዜው እየተመላለሱ የሚያደርሱበትን ጫና መቋቋም ባለመቻሉ አገር ጥሎ መሰደዱን ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡ በመፅሄቱ ሰራተኞቹ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ፍተሻዎች የሚደረጉ ሲሆን፤ ደህንነቶች በቅርቡ ቢሮ ውስጥ በመግባት የተለያዩ መረጃዎችን የያዘ ፍላሽ ዲስክ ሀርድ ዲሰኮች እና ሌሎች ሰነዶችን በኃይል ቀምተው መውሰዳቸውን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛው ከዚህ በፊት ምንም ነገር ቢመጣ ከአገሩ ሳይወጣ በፅናት ለመቆየት እንደሚፈልግ ይናገር የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በቀደመው ፅናቱ የሚያስቀጥል ሁኔታ ስላላገኘ አገሩን ጥሎ መሰደዱን ተናግሯል፡ መፅሄቱ ከተመሰረተ አራት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን የመፅሄቱ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ካሳ ከሀገር ከመሰደዱ በፊት 100ኛ እትሙን ለንባብ ማብቃቱ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ላለፉት 13 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ መቆየቱን ከተጨማሪ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment