Tuesday, March 3, 2015

አስከፊውን ስርዓት ለማስወገድ ጠንካራ የጋራ ትግል ያስፈልጋል!

የኢትዮጵያ ሀዝብ በሕ.ወ.ሓ.ት./ኢሕአዴግ ግፈኛ ስርዓት እየደረሰበት ያለዉ ግፍ እስራትና ግድያ እየተባባሰ መምጣቱ የሚያጠያይቅ ስላልሆነ የመብት የነጻነትና የሀገራችን ሉዓላዊነት ትግል ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ መጠናከር አለበት። ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በተደጋጋሚ አያሌ ጠላቶች አንበርክከዉ ያስረከቡንን ዉድ አገራችን ኢትዮጵያ በተባበረ ክንዳችን ፅናታችንና አንድነታችንን መጠበቅና መከላከል አለብን፡ ዜግነታዊ ግዴታችንም ነዉ። ከዚህ ድንቅ ጀግና ህዝብ ተወልደን ህዝባችን ሲረገጥ ንብረቱ ሲዘረፍ የህግ የፍትህ ያለህ ሲል ከዛም አልፎ ዳር ድንበራችን ሲደፈር ባይተዋር ሆነን ዝም ብሎ መመልከት አግባብነት የሌለዉና አሳፋሪ ድርጊት ነዉ። የኢትዮጵያ ጠላቶች በቛንቛ በጎሳና በሀይማኖት ከፋፍለዉ አርስ በራሳችን ለማጨፋጨፍና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ኣይነቱ ኣካሔዳቸዉን እጅ ለእጅ ተያይዞ በህብረት ተፋልሞ ማክሰምና በምትኩ አንድነትንና መከባበርን ያካተተ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ወኔ መስፈን አለበት። ስለዚህም አገር ኣድን አንቅስቃሴ መደረግ አንዳለበት በፅኑ አናምናለን። የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም የህዝቡን አጀንዳ በማስቀደም የእርስ በርስ ያለመግባባቱን ትተዉ ልዩነታቸዉን እያጠበቡ የመቀራረብና አብሮ የመስራትን እንቅስቃሴ አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ እናሳስባለን። እንዲሁም በመሳሳት በጥቅምና በጭፍን ዘረኝንት ከአረመኔዉ ሕ.ወ.ሓ.ት ጎራ ተሰልፋሁ አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ህገ ወጥ ድርጊቶች በመፈጸም ያላችሁ ሁሉ፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የወያኔ ስርዓት መገርሰሱ አይቀርምና ሀዝባችን በማካሄድ ላይ ያለዉን የመብትና የአገር ሉዓላዊነት የማስከበር ትግል ጎን ትሰለፉ ዘንድ አሁንም ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባልን። ጋሻ ለኢትዮጵያዉያን ይህ የሕ.ወ.ሓ.ት./ኢሕአዴግ አስከፊ አገዛዝ ከስሩ ተነቅሎ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪገነባና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ፍጹም እስኪከበር ድረስ ለትግሉ የምናበረክተዉ አስተዋፅአኦ ይቀጥላል። ኢትዮጵያ በልጆችዋ የተባበረ ሀይል ታፍራና ተከብራ ትኖራለች! 

No comments:

Post a Comment