Thursday, March 19, 2015

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት: ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰቦች ትርፍ ይሠራል የተባለውን የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳደር አስጠነቀቀ -

በደብሩ አስተዳደር እና በሕገ ወጥ ነጋዴዎች የጥቅም ትስስር የቤተ ክርስቲያንን መብትና ምጣኔ ሀብት በሚጎዳ አኳኋን የውል ግዴታዎችን በማፍረስ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው በተጋነነ ዋጋ የተከራዩት የደብሩ መጋዘኖች/ቦታዎች/ በከፊልበደብሩ አስተዳደር እና በሕገ ወጥ ነጋዴዎች የጥቅም ትስስር የቤተ ክርስቲያንን መብትና ምጣኔ ሀብት በሚጎዳ አኳኋን የውል ግዴታዎችን በማፍረስ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው በተጋነነ ዋጋ የተከራዩት የደብሩ መጋዘኖች/ቦታዎች/ በከፊል

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምና የኪራይ ተመን ጉዳዮችን በመፈተሽ የቤተ ክርስቲያንን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ፖሊሲ ለማውጣት የሚያስችል ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ በፓትርያርኩ በተሰጠው መመሪያ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በወርኃ ታኅሣሥ መባቻ የጀመረውን ጥናት እንደቀጠለ ነው፡፡

ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ እና ከሀገረ ስብከቱ በተውጣጡ አምስት የሥራ ሓላፊዎች የተቋቋመው ኮሚቴው በድርጊት መርሐ ግብሩ መሠረት ለጥናቱ ከለያቸው 69 የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት መካከል በሦስት ወራት ቆይታው ከግማሽ በላይ የኾኑትን ሸፍኗል፤ ለተልእኮው ግብዓት ሊኾኑ የሚችሉ መረጃዎችንም በበቂ ኹኔታ እያሰባሰበና እያደራጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

መረጃዎቹ ገዳማቱና አድባራቱ የአምልኮ፣ የመካነ መቃብር እና የልማት በሚል ከተረጋገጡላቸው ይዞታዎቻቸው መካከልበልማት ቦታቸው ውስጥ የተገነቡ የገቢ ማስገኛ ተቋማት የተከራዩበትን ዋጋና የተከራዩበትን ዘመን ጨምሮ የኪራይ ውሎችን አግባብነት በሰነዶች ምርመራና በግምገማ ስልቶች በመፈተሽ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በዘላቂነት የሚደግፉበትን አሠራር ለመቀየስ እንደሚያገልግሉ ተመልክቷል፡፡

ኮሚቴው እስከ አኹን ከአደረገው ማጣራት የተገኙት መረጃዎች፣ የኪራይ ውሎች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች የተጋነነ ትርፍ በሚያመች መልኩ በጥቅም ትስስር እንደሚዘጋጁና በዚኽም ሳቢያ በከፋ መልኩ ለምዝበራ የተጋለጠው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በአሳዛኝ አደጋ ላይ እንደኾነ እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ ከእኒኽም የኪራይ ውሎች ጥቂት የማይባሉት ከሀገረ ስብከቱና ከሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አካላት ዕውቅና እና የወሳኝነት ሚና ውጭ የተፈጸሙ እንደኾኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሰንደቅ ጋዜጣ በዛሬ ዕትሙ፣ በደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደሩ እና በሕገ ወጥ ነጋዴዎች መካከል መኖሩ በተረጋገጠው ግልጽ የጥቅም ግንኙነት ምክንያት የውል ግዴታዎችን በመጣስ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፉ እጅግ በተጋነነ ዋጋ የተከራዩት የደብሩ ይዞታዎች በአደጋ ውስጥ እንደሚገኙ ያስነበበው ዘገባ አንድ ተጨማሪ አስረጅ ነው፡፡

ለራስ አገዝ ልማት እንዲውል ከታሰበው 65‚000 ካሬ ሜትር ይዞታ ውስጥ ከ500 – 1000 ካሬ የሚኾኑ በርካታ ቦታዎችከአካባቢው የገበያ ዋጋ በታች በካሬ ሜትር ብር 2 – 10 ሒሳብ ለመጋዘን፣ ለወፍጮ ቤት፣ ለጋራዥ፣ ለብሎኬት ማምረቻና ለሌሎችም የንግድ ተቋማት ያለጨረታ መከራየታቸው በኮሚቴ ተገልጧል፡፡ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ግለሰቦች ሀብት የሚያፈሩበትና መሬቱን ለግላቸው ማድረግ የሚችሉበት ኹኔታ ተፈጥሯል፤›› የሚለው ኮሚቴው፣ አንዳንዶችም የንግድ ዘርፋቸውን በመቀየር ወደ ኢንዱስትሪነት የሚስፋፉበት ኹኔታ እንደሚስተዋል አስታውቋል፡፡

የደብሩ አስተዳደር ሸንሽኖ ያከራያቸውን ቦታዎች መከታተልና መቆጣጠር እንዳልቻለ ኮሚቴው ጠቅሶ፣ ግለሰብ ነጋዴዎች እጅግ የተጋነነ ትርፍ ሲያገኙ ዝም ብሎ የሚመለከት ሓላፊ ቅን ነው ብሎ ለመገመት እንደማይቻል አሳስቧል፡፡ ቀደም ሲል በስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ላይ እንደ አደረገው ኹሉ፣ የጥናቱን መጠናቀቅ ሳይጠብቅ አስተዳደሩ ሊያርማቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮችም ‹‹በሕጋዊ ሽፋን በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈጸመ ነው፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ ለግለሰብ ነጋዴዎች ትርፋማነት ሌት ተቀን እየሠራ መኾኑን አረጋግጫለኹ›› ያለው የገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኩል ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው አድርጓል፡፡ 

No comments:

Post a Comment