Tuesday, March 3, 2015

ከአምባገነኖች ሽብር እንጂ ዴሞክራሲ አይጠበቅም!

አምባገነኖች በታሪካቸው ሕዝብን ይፈራሉ፤ ሥልጣናቸውን በእጃቸው ለማቆየት ሲሉም ሌሎች አቻዎቻቸው የሄዱበትን ፀረ-ሕዝብ መንገድ ሁሉ ይከተላሉ። በእስያ፣ በምሥራቅ አውሮጳ፣ በአፍሪቃና በላቲን አሜሪካ ሀገሮች ወደ ሥልጣን የመጡ አምባገነኖች ሁሉ በሕዝብ ተገፍተው ከሥልጣናቸው እስኪወገዱ ድረስ፣ ከእነሱ ሀሳብና መስመር የተለዩትን ሁሉ እያሰሩ፣ እያሰቃዩና እየገደሉ ነበር እስከ ሥልጣናቸው መጨረሻ የዘለቁት። በአገራችንም፣ ይህ በሕዝባችን ጫንቃ ላይ በጠመንጃ አፈሙዝ ተፈናጦ፣ በፍርሃት እየተርበደበደ ያለው የህወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነን አገዛዝ፣ እንደሌሎች አቻዎቹ ሁሉ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ጀምሮ ከራሱ አስተሳሰብ ጋር የማይሄዱትን ሲያስርና ሲገድል ቆይቷል። ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላም፣ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና ግለሰቦችን አስሯል፤ ገድሏል፤ ከአገር እንዲሰደዱም አድርጓል። በራሱ ሳምባ የሚተነፍሱ የድርጅት አመራሮችን ሳይቀር እንኳን ገድሏል፤ ከሥራ አባሯል፤ በሌሎች ድርጅቶች ስም ለራሱ የሚያገለግሉ የካድሬዎች ጥርቅም ድርጅትም ፈጥሯል። ለምሳሌ በቅንጅት ስም ሌላ ተለጣፊ ድርጅት ፈጥሮ መገልገያ መሳሪያው ማድረጉ የቅርብ ትውስታችን ነው። እራሱ ጻፍሁት በሚለው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 30 በነፃ የመደራጀትና ሐሳብን የመግለጽ መብት ለሁሉም ዜጎች እንደሚፈቅድ እየገለጸ፣ ይህንኑ አንቀጽ ቀድሞ የሚሽረው ግን እራሱ አምባገነኑ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ነው። 

No comments:

Post a Comment