Sunday, March 15, 2015

የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ – ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን -

ከርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት
ቀን፡ መጋቢት 5 2007 ዓ/ም (14/03/2015)
ሕዝብ መርጦ በቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ስልጣን ላይ ያስቀመጣቸው ጥቂት ካህናት ለስጋዊ ጥቅም በማደር ለሥልጣንና ለንዋይ ሲሉ በፈጠሩት ችግር ምክንያት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ላለፉት ሁለት ዓመታት በብዙ ችግሮች ውስጥ ካለፉ በኋላ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍትሐዊ ውሳኔ ያገኝ ዘንድ ሂደቱ መጀምሩ የሚታወቅ ነው።
በዚህ መሠረት እነዚህ ህዝብን ከድተው ለዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በማደር ሕዝብ በሃብቱና በጉልበቱ ጥሮና ግሮ ያፈራውን የቤተ ክርስቲያን ንብረት የቅዱስ ሲኖዶስ ሃብትና ንብረት ነው በሚል ሰበብ በመቀራመት ሹመትና ሽልማትን ለማግኘት ሲሉ ያነሱት ዋናው የባለቤትነት ጥያቄ ውዝግብ የፍርድ ቤት ብይን እስከሚያገኝ ድረስ አባላት ገንዘብና ጉልበታቸውን አስተባብረው በገዙት ህንፃ ቤተ ክርስቲያን በእኩልነት የመገልገል መብት ስላላቸው ይህ የመብት ጥያቄ በሃገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት በኩል ምላሽ ማግኘት ነበረበት።
London_Ethiopian_Church-625x370
ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን
ይህንን ተከትሎ ጊዚያዊ የፍትሕ መመሪያ (Interim relief Order) እንዲያወጣ ከቤተ ክርስቲያኑ አባላት ማመልከቻ የቀረበለት ጉዳዩ የሚመለከተው የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ የአስተዳደር ሥልጣን አንለቅም ብለው ችግር የፈጠሩት ካህናትን የሚከተሉት ባብዛኛው የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑትና በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባልነት መብታችን ይከበር በማለት በመታገል ላይ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ አባላት አንዱ በድንኳን ውስጥ፤ ሌላው ደግሞ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሆኖ አገልግሎት ማግኘታቸው ፍትሐዊ አለመሆኑን በመረዳት ሁለቱም ወገን ተራ ገብቶ በቤተ ክርስቲያኑ ሃብትና ንብረት እንዲገለገል በ13/03/2015 የሕግ ማዘዣ (የInterim relief order) ሊያወጣ ችሏል።
ሆኖም ግን ይህንን የከፍተኛው ፍርድቤት ትዕዛዝ ተፈጻሚ ማድረግ የሚገባቸው እነዚሁ ሕገ ወጥና ሥርዓተ አርበኛ ካህናትና ተከታዮቻቸው፤ ፍርድ ቤቱ ከቁልፍ ማስረከብ ጀምሮ ስለ አፈጻጸሙ በዝርዝር ያስቀመጠውን ትዕዛዝ ሁሉ በመጣስ አባላት በቤተ ክርስቲያኗ መጠቀም በሚገባቸው ተራ ቤተ ክርስቲያኑን ዘግተው ከመሰወራቸውም በተጨማሪ በተቀረው ዕለተ ሰንበትና በአዘቦቱ ቀን ጭምር ቤተ ክርስቲያኑን ለራሳቸው ተከታዮች ብቻ እንዳሻቸው በመክፈትና በመዝጋት መገልገላቸውን ቀጠሉበት።
እነዚህ የእውነታውን ዓለም አንቀበልም በማለት ራሳቸው በፈጠሩት ዓለም መኖር የጀመሩ ሕገ ወጥ ግለሰቦች፤ በቤተ ክርስቲያኑ አባላት ላይ የፈጸሙት በደልና የፈጠሩት ችግር አልበቃ ብሏቸው ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ከእንግሊዝ የፍትሕ ሥርዓት ጋርም በመላተም እያደረሱ ያሉት የሕግ ጥሰትና ሥርዓተ አልበኝነት የሕግ በትር ሳያርፍባቸው ለመታረም የማይችሉ እብሪተኞች መሆናቸውን አስመስክሯል።
ሀገረ እንግሊዝ የሕግ የበላይነት የሰፈነበትና ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ዳኞች ከማንግሥትም ሆነ ከማንኛቸውም አካል ተጽዕኖ ሳይኖርባቸው በነጻነት ፍትሐዊ ፍርድን የሚሰጡበት ሃገር በመሆኗ እነዚህ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ያልፈጸሙ ሰዎች በፈጸሙት የሕግ ጥሰት ወንጀል (Contempt of Court) ተከሰው በ12/03/2015 በከፍተኛው ፍርድ ቤት ለCommittal hearing እንዲቀርቡ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሊወጣባቸው ችሏል።
በContempt of Court ተከሰው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የፍርድ ቤት መጥሪያ የተላከላቸው 4ቱ ቤተ ክርስቲያኗን የአስተዳደር ሥልጣን አንለቅም ያሉ ካህናትና በ2013 ዓ/ም እነሱ መርጠው የሾሟቸው ሌሎች 5 ምእመናን በድምሩ 9 ሕገ ወጥ ግለሰቦች የፍርድ ቤቱን መጥሪያ ላለመቀበል ሲሉ በየስርቻው ለመደበቅና ለመሸሽ ቢሞክሩም የፍርድ ቤት መጥሪያ አከፋፋዮቹ ያላቸውን ልዩ ልዩ ሕጋዊ ዘዴ ተሞክሮዎችን ተጠቅመው ማዘዣውን ለተከሳሾቹ ማድረሳቸውን ለድርድ ቤቱ በማረጋገጣቸው ፍርድ ቤቱ ማዘዣው ለተከሳሾቹ መድረሱን በመቀበል የCommittal hearing የፍርድ ቤት ሂደት በ12/03/2015 እንዲካሄድ አደረገ። በፍርድ ቤቱ መጥሪያ መሠረት ዘጠኙ ተከሳሽ (Defendant) ግለሰቦች ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው አንዱ ብቻ እወክላቸዋለሁ ከሚል አንድ ጠበቃ ነኝ ባይ ጋር ሲገኝ የተቀሩት 8 ተከሳሾች የፍርድ ቤቱን መጥሪያ ጥሰው ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
እነዚህ በሃሰትና በቅጥፈት ሰውን ከማሳሳት አልፈው ራሳቸውንም የሚያታልሉ ግለሰቦች የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ እስከደረሰበት ቀን ድረስ ይግባኝ ስለጠየቅን ቁልፍ ለመስጠት በሕግ አንገደድም፤ ሲኖዶሱ ጽፏል፤ ምንም የሚመጣ ችግር የለም ወ.ዘ.ተ እያሉ የተለመደውን የማወናበድና የማጭበርበር ተግባር ሲያከናውኑ የከረሙ ቢሆንም ይህ የቅጥፈት ድርጊታችው ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለመፈጸም በContempt of Court ክስ ከመከሰስ አላዳናቸውም።
ይህም ብቻ አይደለም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ቤተ ክርስቲያን መሥርተው በፍቅርና በመተሳሰብ በሰላምና በደስታ ይኖሩ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርሳቸው ለማናከስና ለማበጣበጥ በዘረኛው ወያኔ ተሹመው ወደ ለንደን የመጡት አቡነ እንጦስ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን አውቶብስ ተከራይተው በየቤተ ክርስቲያኑ በማቅረብ ከቅዳሴ የሚወጣውን ሰው ተሳፈር በማለት የወያኔ ተከታይ ካህናትን በመጨምር ለታቦት የሚጠላ ጥላ በማስያዝ በእንግሊዝ ፍትሕ ሚኒስቴር ግንብ ዙሪያ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተቃውመዋል።
አቡነ እንጦስም እግዚአብሔርን ሳይፈሩና ሰውን ሳያፍሩ የሰልፉ ተዋናኝ በመሆን የሌሎች ክርስቲያኖችን በቤተ ክርስቲያናቸው ገብተው መጸለይን አጥብቀው ሊቃሙ ችለዋል። ይህንንም የወያኔ ተልኳቸውን ሪፖርት ወደ አዲስ አበባ በመላክ የተለመደው የወያኔ የሃሰትና የቅጥፈት ታሪክ ታክሎበት በኢትዮጵያ ሕዝብ በተጠላውና በተናቀው የወያኔ ሥርዓት የሃሰት ፕሮፓጋንዳው ማሰራጫ ባደረገው የኢትዮጵያ ቴላቪዥን በዋና ዜናነት ተላለፈ።
ይህ ሁሉ ሆያ ሆዬ ግን የፍትሑን ሥርዓት ሂደት መግታት ቀርቶ ሊያዘገየውም ስለማይችል ፍርድ ቤቱ በተቀጠረበት በዕለተ ሐሙስ 12/03/2015 ችሎቱን የCommittal hearing ሂደቱ ሊቀጥል ችሏል። የፍርዱ ችሎት እንደተጀመረም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ የአመልካቾቹንና የተካላካዮቹን ጠበቆች ቃል ካዳመጠና አጠቃላይ ጉዳዩን ከተገነዘበ በኋላ የሚከትለውን የፍርድ ውሳኔ አስተላልፏል።
1. የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ በ13/02/2013 የበየነው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ Interim relief order ተፈጻሚ መሆን አለበት፤
2. ፍርዱንና ትዕዛዙን አለመፈጸም ለከፍተኛ ቅጣት ይዳርጋል።
3. ለ Committal hearing የተሰየመው ፍርድ ቤት ከፍተኛው የፍርድ ቤት አስቀድሞ ያወጣውን ትዕዛዝ በማይፈጽም ላይ እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እስር የመፍረድ ሥልጣን ስላለው የከፍተኛው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያለ አንዳች ማወላወል መፈጸም ይኖርበታል።
4. የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የሚያስቆም የላቀ ፍርድ ቤት ማገጃ እስካልወጣ ድረስ ይግባኝ ብያለው (Appeal) አድርጌአለሁ በማለት የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አለመፈጸም አይቻልም::
5. የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሳይፈጸም በዘገየ ቁጥር ቅጣትና ፍርዱም እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል።
6. በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት መጪው ቅዳሜ የአመልካቾች (የClaimant)ተራ ስለሚሆን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የወጣውን ዝርዝር መመሪያ ተከትሎ አባላት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመግባት ቅዱስ ታቦቱ ባለበት እንዲያገለግሉና እንዲገለገሉ ይደረግ፤ ይህ ሳይፈጸም ቢቀር ግን ሁኔታው እጅግ ወደ ከፋና ጠነከረ ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል።
7. ተከሳሾቹ ይግባኝ ፍቃድ ይሰጣቸው ዘንድ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የይግባኝ ፍቃድ ያገኙ ዘንድ (ለppeal Court) ማመልከት ይችላሉ፤ ፍቃድም ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል ነገር ግን ይህ በምንም መንገድ ሕጉን ሊለውጥ አይችልም።
8. ተከሳሾቹ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሳሳተ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለመረዳት ተችሏል፤ ነገር ግን ይህ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ላለመፈጸም ምክንያት ሊሆን አይችልም።
9. ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ብይን ከማሳለፉ በፊት ተከሳሾቹ ሕጋዊ እውቅና ባለው ባለሙያ ጠበቃ (Professional Lawyer) በመወከል የቀረበባቸውን Contempt of Court ክስ መከራከር እንደሚገባቸው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሕግ ስለሚያዝ እስከ 19/03/2015 ድረስ ሕጋዊ ጠበቃ በመያዝ ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቁ፤ የጠበቃውንም ወጪ ለመሸፈን ለLegal aid እንዲያመለክቱ።
10. ቀጣዩ የፍርድ ቤት ችሎት hearing በ26/03/2015 እንዲሆን፤ በዕለቱም ሁሉም ተከሳሾች እንዲቀርቡ፤ ካልቀርቡ ግን 1ኛ) በሌሉብት እንደሚፈረድባቸው፤ 2ኛ) የእስር ማዘዣ ወጥቶ ታስረው እንዲቀርቡ እንደሚደረግ።
11. በዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔና ዳኛው በሰጡት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሠረት ተከሳሾቹ ሐሙስ 12/03/2015 የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍ ለአመልካቾች (Claimant) ጠበቃ መስጠት ስለሚገባቸው የአመልካቾች ጠበቃ ቁልፉን እንዲያስረክቡ ለተከሳሾቹ መልዕት ቢልክላቸውም ሳይተባበሩ ቀርተዋል። ጠበቆቹም የሕግን ረቂቅነትና ክብደት ስለሚረዱ በተከሳሾቹ ላይ ሊመጣ የሚችለውን ቅጣት በማጤን ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት ሲሉ በማግስቱ ዓርብም ቁልፉን እንዲያቀብላቸው ሌላ ማሳሰቢያ መልዕት ቢልኩላቸውም በእንቢተኝነቱና በሕገ ወጥነቱ ቀጥለውበት ይገኛሉ።
ማንም ክርስቲያን ለወገኑ ክፉ ማሰብና መመኘት አይገባውም፣ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የሁሉም ባለቤት፤ የሁሉም ዳኛ የሆነውና ልብና ኩላሊት መርምሮ የሚያውቀውን ሃያሉን ልዑል እግዚአብሔርን ሳይፈሩ እውነቱ የት እንዳለ እያወቁና ሂሊናቸው በሚገባ እየተረዳው ሃዘንና ርህራሄ በሌለው ጭካኔ ውስጥ ገብተው ክፋትና ተንኮልን በመፈጸም ሕዝብን የበደሉ በመሆናቸው የሕግን በትር ቀምሰው ካልሆነ በስተቀር ተምረው የሚመለሱ አይደሉም። አቡነ እንጦስና ሌሎች የዲያስፖራውን ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮችን ሰላማዊ ህይወት ለመበጥበጥ በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ተልከው የመጡትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብትን በመጣስና በመርገጥ ዓለም የሚያውቀውን የዘረኛ አገዛዝ ፖለቲካ ወደ ውጪ በማምጣት የሚፈጽሙት የሽብር ተግባር በማስረጃ ሲረጋገጥባቸው እጃቸው እየተያዘ ለፍርድ በመቅረብ አስፈላጊው ብይን የሚተላለፍባቸው ይሆናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
ከርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት።

No comments:

Post a Comment