Wednesday, February 25, 2015

አቶ ግርማ በምርጫው ተስፋ ቆርጠዋል

አቶ ግርማ  በምርጫው ተስፋ ቆርጠዋልሰማያዊ ፓርቲ የገባ የአንድነት አመራር የለም 
ለኢህአዴጎች ትክክለኛውን የህዝብ ስሜት ነግሬአቸዋለሁ 
ለ“አንድነት” ችግር የመጀመሪያው ተጠያቂ መንግስት ነው

በ2002 ምርጫ አሸንፈው ፓርላማ የገቡት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን ለእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ ማፅደቁን ተከትሎ በዘንድሮ ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገለፁ፡፡ 
ቦርዱ አንድነትን በተመለከተ የሰጠውን ውሳኔ ክፉኛ የሚተቹት አቶ ግርማ፤ በግንቦቱ ምርጫ ዙሪያና የፓርላማ ቆይታቸውን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ 



በርካታ የአንድነት አመራር አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ገብተዋል ተብሏል፤ እርስዎ ለምን ፓርቲውን አልተቀላቀሉም? ከዚህ በኋላ የእርስዎ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫ ምንድን ነው የሚሆነው?
በርካታ የአንድነት አመራር አባላት ወደ “ሰማያዊ” ገብተዋል የሚለው ስህተት ነው፡፡ አንድም የካቢኔ አባል የነበር ሰው ወደ ፓርቲው አልገባም፡፡ የፈለገ ሰው ግን ያሻውን  ፓርቲ መቀላቀል እንደሚችል አቅጣጫ አስቀምጠናል። መንግስት አንድነት ላይ እንዲህ ያለ “ነውረኛ” እርምጃ ከመውሰዱም በፊት ቢሆን ሰዎች ወደ ፈለጉት ፓርቲ መሄድ ይችሉ ነበር፡፡ አሁን መንግስት በያዘው አካሄድ የመድብለ ፓርቲ ስርአት መሸከም የሚችል መንግስታዊ መዋቅርም ሆነ ፍላጎት የለም፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግሉ በምን አይነት መንገድ ሲመራ የተሻለ ለውጥ ያመጣል የሚለውን አስበንበት አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለብን ወስነናል፡፡ 
ፓርቲውን ያልተቀላቀላችሁበት ምክንያት ምንድንነው?
ሰማያዊ ፓርቲ ገብተን ብናጠናክረው፣ ሲጠናከር እግሩን የሚቆርጡት ከሆነ ትርፉ አጉል ድካም ነው የሚሆነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የሊበራል አስተሳሰብ  የሚከተል እንደመሆኑ የግለሰቦችን መብት ያከብራል፡፡ የፈለገ ሰው ወደ ፈለገው ፓርቲ የመግባት መብት አለው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ወደ ሰማያዊ ገብተዋል የሚለው ፖለቲካ ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም፡፡ ከኛ አመራር ውስጥ ግን ማንም የስራ አስፈፃሚ  አባል ወደ ሰማያዊ አለመግባቱን አረጋግጣለሁ። ይሄ ለሰማያዊ ከጠቀመውና የኢትዮጵያን  የፖለቲካ ሁኔታ ማሻሻል የሚችል ከሆነ በኛ በኩል ቅሬታ የለንም፡፡ 
አንድነትን ያለአግባብ “ተነጥቀናል” የምትሉ አመራሮች ምንድን ነው ያሰባችሁት? 
አስር ጊዜ እየተፈተነ የሚወድቅ የፍትህ ስርአት ቢኖረንም የፍትህ ስርአቱን ለመፈተሽ ፍ/ቤት ሄደናል፡፡ ፍ/ቤቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው የሚሰጠው ወይንስ ማስረጃን ተንተርሶ ነው የሚወስነው የሚለውን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ጉዳያችንን ግን ፍ/ቤት አቅርበናል፡፡ ፍ/ቤቱ ትክክለኛ ውሳኔ የሚወስን ከሆነ፣ እኛ ከ2007 ምርጫ ጋር ምንም የተለየ ፍቅር የለንም። ፓርቲያችንን በተሻለ ሁኔታ በመምራት፣ እንደነ ትዕግስቱ አይነት “ሰንኮፎችን” የነቀልንበት ሂደት አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ 
በሌላ በኩል ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ጋር ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንዳናጠፋ የተፈጠረ እድልም ሊሆን ይችላል፡፡ ለወደፊት የሰላማዊ ትግሉን ለማጥራት የሚረዳ አጋጣሚ ነው ብዬም እቀበለዋለሁ፤ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በመንግስት ደረጃ እንዲህ ዓይነት “አስነዋሪ” ድርጊት ሲፈፀም ማየትና የዚያ አካል መሆን በጣም ያሳፍራል፡፡ ሁሉም የሚያፍሩ ይመስለኛል፣ ካላፈሩ ደግሞ ህሊና አላቸው ብዬ አላስብም፡፡ በኛ በኩል ግን ባደረግነው ሁሉ ምንም የሚቆጨን ነገር የለም፡፡ በነገራችን ላይ ሲጀመር አንስቶ “ውጤቱን በኋላ ታዩታላችሁ” እያለ ትዕግስቱ ሲያስፈራራን ነበር፤ ስለዚህ እሱ ጨዋታ ውስጥ የገባው ውጤቱን አውቆት ነው፤ እኛ ግን ጊዜና ገንዘባችንን እያባከንን ነበር፡፡ 
አንድነት ውስጥ በየጊዜው “ደንብና መርህ ይከበር” የሚሉ ውዝግቦች መከሰታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው? 
በ2002 ምርጫና አሁን የተደረገው ተመሳሳይ ነገር ነው፤ ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡ በ2002 በተፈጠረው ሁኔታ መንግስት አንድነትን ለእነ ፕሮፌሰር መስፍን ወይስ ለእነ ኢንጅነር ግዛቸው ብሰጥ ይሻላል የሚል ምርጫ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ለኢ/ር ግዛቸው ብሰጠው ይሻላል ብሎ ወሰነ፡፡ አሁን ደግሞ ከእነ በላይ እና ከእነ ትዕግስቱ የቱ ይሻላል ብሎ መረጠ፡፡ ለትዕግስቱ ተሰጠው፡፡ 
በ2002 ውሳኔ አሰጣጣቸው ላይ  በጣም ጠንቃቃ ነበሩ፤ አሁን ደግሞ ምንም ቀዳዳ ሊያገኙ ስላልቻሉ በጣም አሳፋሪ የሆነ ውሳኔ ወሰኑ፡፡ ለምንድን ነው አንድነት ላይ እንዲህ የሚደረገው? ምንም ጥርጥር የለውም፤ አንድነት አስቦ የሚሰራ ፓርቲ በመሆኑ ነው፡፡ በሳምንት ሁለት ጋዜጣ ያሳትማል፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ሁለት ጋዜጣ በሳምንት አያትምም፡፡ ሁለት ጋዜጣ የሚያሳትም ፓርቲን ኢህአዴግ እንዴት አድርጎ መቋቋም ይችላል? እኛ የሚዲያ ቅስቀሳና ክርክር ሲጀምር እንደምንበልጣቸው እርግጠኞች ነበሩ፤ ስለዚህ ይሄን ቡድን ማፍረስ ነበረባቸው፡፡ 13 ያህል የብሮድካስትና ፕሪንት ባለሙያዎችን አዘጋጅተን  ስንጠብቃቸው ነበር፤ ይሄ ያስደነግጣቸዋል፡፡ 
ሌላው እስከ 500 እጩዎች አቀርባለሁ ብሎ የተዘጋጀ ፓርቲ የለም፡፡ አብዛኞቹ ይሄን የማድረግ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ህዝቡ ጋ ተደራሽ ሆኖ፣ ፓርቲው ባለው ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ባለው ደካማ አስተዳደር የሚፈጠረውን የተቃውሞ ድምፅ ሊሰበስብ የሚችለው አንድነት ብቻ እንደሆነ ኢህአዴግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በእርግጥም ይሄን ማድረግ የሚችለው አንድነት ብቻ ነበር፡፡ ታዲያ ይሄን ኃይል ፈርተው ካላፈረሱ ምን ሊያፈርሱ ይችላሉ? በ2002 ዓ.ም ተመሳሳይ ነገር ነው ያደረጉት፡፡ የመድረክ ጥንካሬ የነበረውን አንድነት ማተራመስ፣ መድረክን ለማተራመስ ይጠቅማቸው ስለነበር ያንን አድርገዋል፡፡ አሁን መድረክን ለምን አይነኩትም? በኛ ሰበብ ነበር መድረክን ሲጨፈጭፉ የነበሩት፤ ስለዚህ አንድነትን ለማዳከም በቂ ምክንያት ነበራቸው፡፡ 
እርስዎ በአንድነት ውስጥ ለተፈጠረው ምስቅልቅል የመጀመሪያ ተጠያቂ የሚያደርጉት ማንን ነው?
ምንም ጥርጥር የለውም መንግስትን ነው። የደህንነት አካሉ ነው ይሄን ያደረገው።  ኃላፊነቱን በመውሰድ ያስፈፀሙት ደግሞ ምርጫ ቦርድና ሚዲያዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ተኩስ የተጀመረው በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ ነው - ከኮሙኒኬሽን የሚታዘዝ ግለሰብ አንድም ነገር ሳይኖር “አንድነት እየተከፋፈለ ነው” ብሎ ፃፈ፡፡ ከዚያ ሬዲዮ ፋና፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሌሎች ሚዲያዎች ተግተውበታል፡፡ እኛ መልስ እንስጥ ብንል ተቆርጦ ተቀጥሎ ነው የሚቀርበው፡፡ ለሬዲዮ ፋና ለምንድን ነው መልስ እማትሰጡት ተብለን መልስ ስንሰጥ፣ በቪዲዮ በተደራጀ መልኩ ቀርፆ ከኢቢሲ ጋር ግንባር በመፍጠር በአካል ያልተገናኘን ሰዎችን ስንከራከርና ስንሰዳደብ እንደነበር አድርጎ አቅርቧል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን የአባላት ምልመላችን “ሆዳሞችን” እንዳያፈራ መጠንቀቅ እንዳለብን  ተረድተናል፡፡ ከብዙ ሺህ አባላት ሦስትና እና አራት “ሆዳሞች” ቢኖሩ የሚገርም ባይሆንም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡ 
መድረክን ወክለው ነው ፓርላማ የገቡት። ከእዚህ አንፃር ለምርጫው በፓርላማ መቀመጫ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ መድረክ ይጠቀምበታል? 
 መድረክን ወክዬ ነው የገባሁት፤ ስለዚህ ይችላል፡፡ በእርግጥ መድረክን ወክዬ ከተወዳደርኩ በኋላ የህዝብ ወኪል ነው የሆንኩት፡፡ ካልሆነ “አንድነት” ከመድረክ ሲወጣ “ግርማ የመድረክ ተወካዩ አይደለም” ወይም የወረዳ 6 ሰዎች “ግርማ የመድረክ ተወካይ ካልሆነ አንፈልገውም” ብለው ፊርማ ማስገባት ቢፈለጉ ማስተባበር የሚችለው መድረክ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በፓርቲ ጥቅማ ጥቅም ደረጃ መድረክ የሚጠቀም ይመስለኛል፡፡ 
ላለፉት አምስት ዓመታት በፓርላማ ብቸኛ የተቃዋሚ በፓርላማ ቆይታዎ የሚጠበቅብኝን  ተወጥቻለሁ ብለው ያስባሉ?
 እኔ በህይወቴ ከወሰንኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ የማይቆጨኝ ፓርላማ ለመግባት የወሰንኩት ውሳኔ ነው፡፡ ያደረግሁት አስተዋፅኦ አደርገዋለሁ ብዬ ከገመትኩት በላይ ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን አነብ ነበር፤ የማነበው የሚጠበቅብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ነው፡፡ መደገፍ ያለብኝን ለመደገፍ፣ የህዝብ ጥያቄ ነው ያልኩትን ለመጠየቅ፡፡ እናም በኔ በኩል ብዙ ደክሜያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሉም የም/ቤቱ አባላት ይሄን ያደርጋሉ ወይ ካልከኝ አያደርጉም፡፡ ምክንያቱም ምንም የሚጠየቁበት ነገር ስለሌላቸው ኃላፊነት የለባቸውም፡፡ 
አንድ ሰው ብቻውን ፓርላማ ውስጥ መቆየት በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደ አንድ ሰው ሳይሆን እንደ ሺህ ሆኜ ሰርቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ስገባም አዋጅ ላፀድቅ ወይም ለመረጠኝ ህዝብ መሰረተ ልማት ላሟላ አልነበረም - አማራጮችን ለማቅረብና የህዝቡን ስሜት ለማስተጋባት ነው። እስካሁን ካገኘሁት አስተያየት የአብዛኛው ህዝብ ድምፅ ሆኜ አገልግያለሁ ብዬ አምናለሁ። ለኢህአዴጎች ትክክለኛውን የህዝብ ስሜት ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ተጠቅመውበታል ወይ ከተባለ አልተጠቀሙበትም ምክንያቱም እነሱ የሚሰሙ ሰዎች አይደሉም፡፡ 
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስንም ሆነ አቶ ኃይለማርያምን በጥያቄ የመሞገት ዕድል ነበርዎት፡፡ ከሁለቱ የትኛው የተሻለ አሳማኝ ምላሽ ይሰጥዎት  ነበር? በአጠቃላይ ሃገር በመምራት ረገድስ…
ሁለቱም ለህዝብ ምላሽ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ ለጥያቄም ምላሽ አይሰጡም፡፡ ግን ቢያንስ መለስ ጥያቄ ሲመልስ ብልጥ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ አቶ ኃይለማርያም ባለፈው ጥያቄ ሲመልሱ “ባለኝ መረጃ መሰረት” እያሉ ነነር፤ እርግጠኛ ባልሆኑበት መረጃ ሃገር እያስተዳደሩ ነው፡፡ በኔ እምነት መለስ በከፍተኛ ስልጣን ነበር የሚመራው፡፡ ኃይለማርያም ያ ስልጣን አላቸው ብዬ አላስብም፡፡ 
አንድነትን የመሳሰሉ ትላልቅ ፓርቲዎች “ፅንፍ በመያዝ ገዥው ፓርቲ ጥላቻ እንዲያድርበት ይገፋፉታል” የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ አንድነት ከጥላቻ ፈፅሞ ነፃ የሆነ ፓርቲ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ እኔ እንደውም የምታማው ለኢህአዴግ ቅርብ ሆኗል እየተባልኩ ነው፡፡ አንድነት ውስጥ ቂም በቀልና ስድብ የለም፡፡ በተለይ የአሁኑ አሰራራችን የሰለጠነ ነበር፡፡ አንድ ጓደኛዬ፤ “ኢህአዴግ ከሚዲያዎች ‹አዲስ ነገር› ጋዜጣን ከፓርቲዎች ‹አንድነትን› መሸከም ካቃተው የፖለቲካ ጨዋታ አይችልም ማለት ነው” ብሎ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ነፃ ሚዲያና የመድብለ ፓርቲ ስርአት መሸከም የማይችል እንደሆነ የሚያረጋግጠው ይሄ ነው። ለምርጫው ስትራቴጂና ፕላን አውጥተን ኢህአዴጐችን በግልፅ በዚህ መንገድ ነው የምናሸንፋችሁ ያልነው እኛ ብቻ ነን፡፡ የጥላቻ ፖለቲካን እናስወግዳለን ብለን ነበር ስንሰራ የቆየነው፡፡ 
ከዘንድሮ ምርጫ  ምን ይጠብቃሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ  የሚባል አለ? እኔ ምርጫው አልቋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው የሃብት ብክነት ነው፡፡ አንድም መንግስት ለመሆን የሚያስችላቸውን እጩዎች ያላቀረቡ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት ምርጫ‘ኮ ነው፡፡ ለሁለት ወንበር የሚወዳደሩ ፓርቲዎች አሉ፤ እነዚህ በቃ አላማቸው ፓርላማ መግባት ብቻ ነው፡፡ እንደ ፓርቲ የሚወዳደሩትም እንኳ ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ አያሸንፉም እንጂ ቢያሸንፉ መንግስት አይሆኑም፡፡ መንግስት ለመሆን ሳያስቡ መወዳደር ምን ማለት ነው? ስለዚህ ኢህአዴግ መንግስት እንደሚሆን አረጋግጧል፡፡ 
በእርስዎ አመለካከት፣ አሁን ባለው የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ ይቻላል?
እኛ በምርጫ እምነት ነበረን፡፡ ህዝቡ “ስልጣን ለእገሌ ሰጥቻለሁ፤ እሱ ይምራኝ” የሚለው በምርጫ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ስልጡን መንገድ ግን እየተጭበረበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እኮ ከማይችሉት ቡድኖች ጋር እየተጋጠመ በማሸነፍ የዋንጫ ጥማቱን ማርካት ይችላል። ጥንካሬና ጉብዝና የሚለካው ከሚመጥኑት ቡድን ጋር ሲወዳደሩ ነው፡፡ ያለዚያ አነስተኛ ኪሎ ያለውን ቡድን መርጠህ በዝረራ እያሸነፍክ  ሁሌም ሜዳሊያ መውሰድ ትችላለህ፡፡ 
ምርጫ ስልጡን መንገድ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ ይሄንን ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡ እነዚህ ሰዎች በምርጫ አልጫወትም ካሉ፣ ህዝቡ በሌላ መንገድ  እሞክራቸዋለሁ ሊል ይችላል፡፡ አብዮት ግን በእቅድ የሚመራ አይደለም፤ ሁሉን እንዳልነበረ የሚያደርግ ነው፡፡ አብዮት በዕቅድ የሚመራ ቢሆን እኔ እመራ ነበር፡፡ 
ጥያቄዬን አልመለሱልኝም፡፡ እምነት አሁን ባለው ሁኔታ  በምርጫ ስልጣን መያዝ ይቻላል አይቻልም? 
የ2007 ምርጫ እኮ አበቃ!
ለወደፊትስ? 
እርሱን እንግዲህ እኔ ጠንቋይ አይደለሁ፤ በምን አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን አንዱ ተስፋህ እየጨለመብህ ሲሄድ ሌሎች የሚለመልሙ ተስፋዎች ይኖራሉ፡፡ እኔ በበኩሌ፤ ስልጡኑ መንገድ ምርጫ ብቻ ነው የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፤ ግን ሰይጣናዊ መንገድም አለ። በሰይጣናዊ መንገድ ሲሆን መሳሪያ ያድነኛል ማለት አያስኬድም፤ ሙባረክና ጋዳፊንም አላዳናቸውም፡፡    

No comments:

Post a Comment