Saturday, November 28, 2015

ከመጠምጠም መማር ይቅደም | መስፍን ወልደ ማርያም [ፕሮፌሰር]

mesfinኅዳር 2008 በፌስቡክ የምንሰባሰበው ለመወያየት፣ አንዱ ከሌላው እንዲማር፣ መረጃዎችን በነጻነት እንድንለዋወጥ፣ ይህንን ሁሉ በማድረግ ራሳችንን ለማሻሻል፣ የእኛ መሻሻል እየተራባና እየተባዛ የአገርና የሕዝብ መሻሻል እንዲሆን፣ ከተቻለንም ከአገራችንና ከሕዝባችን አልፈን የምንታይ የዓለም አካል እንድንሆን መስሎኝ ነበር፤ ሳየው በዚያ መንገድ ላይ ያለንና ፌስቡክን ለበጎ ዓላማ እየተጠቀምንበት ያለን አይመስለኝም፤ ስለዚህ ወይ መታረም፣ አለዚያም በፌስቢክ ጊዜ ማጥፋቱን መተው ምርጫ ሊሆንብን ነው፡፡ ምናልባት 99.99% በእኔ ሰፈር ያሉ የፌስቡክ ተሳታፊዎች ወደፌስቡክ የሚገቡት ለመናገር ነው፤ መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱት ጥቂት አይደሉም፤ ካልተናገሩ የሌሉ ይመስላቸዋል፤ ዋናው ነገር መናገር ይሆንና የሚናገሩት ነገር ወይም ጉዳይ ሌላው ቀድሞ ከተናገረው ጋር የሚያያዝ (የሚቃወመው ወይም የሚደግፈው) ሳይሆን ፈጽሞ ወደተለየ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ አዲስ ርእስ መክፈት የተለመደ ነው፤ የአብዛኛው ፍላጎት ማስተማር ወይም ማሳወቅ ነው፤ ማስተማር ወይም ማሳወቅ ቀላል ነው፤ መናገር የሚችል ወይም ፊደሉን አውቆ መጻፍ የሚችል ማስተማር ይችላል፡፡ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በጃንሆይ ዘመን ትልቅ ሚኒስትር ነበር፤ በደርግ ዘመን ለብዙ ዓመታት ታስሮ ሲወጣ ሥራ አልነበረውም፤ ችሎታውን ስለማውቅ በዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምር አመቻቸሁለትና ማስተማር ጀመረ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ስንገናኝ ‹‹እኔ ማስተማር ቀላልና እረፍት የሞላበት ሥራ ይመስለኝ ነበር፤ ለካ አንቅልፍ የሚያሳጣ ነው! እዝናናለሁ ባልሁ ቁጥር አንድ ክፍል ሙሉ ተማሪዎች ተሰብስበው ዓይኖቻቸውን እያቁለጨለጩ ምን እንደማስተምራቸው ሲጠብቁ ይታዩኛል! እረፍት ይነሡኛል!›› አለኝ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ማስተማሩን ተወ፤ ኅሊና ላለው ሰው ማስተማር ቀልድ አይደለም፤ ያደክማል፤ ለማስተማር መማር ያስፈልጋል፤ ለማሳወቅ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ከመማር ይልቅ ማስተማር፣ ለማወቅ ከመጣር ይልቅ ለማሳወቅ መጣር የሚቀልለው ሰው የእውቀት ሰው አይደለም፤ ሌላ ሥራ ቢመርጥ ይሻለዋል፡፡ ሳያውቁ ለማሳወቅ አደባባይ መውጣት ከችኮላ ወይም ከስንፍና፣ ከትዕቢት ወይም ከግዴለሽነት የሚመጣ ነገር ይመስለኛል፤ ውሎ አድሮ ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም፤ በአደባባይ መናገር ወይም መጻፍ የመጨረሻው መጋለጥ ነው፤ በአደባባይ መናገርና መጻፍ በሕዝብ ፊት መጋለጥ መሆኑን ብዙ ሰዎች አያውቁም፤ በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ሰዎች ይህንን መጋለጥ ፈርተውትና ሸሽተውት የሚርቁት አሉ፤ መጋለጥን ፈርተው ዓይኖቻቸውን ዘግተው፣ ጆሮዎቻቸውን ደፍነው፣ አፋቸውን ለምግብና ለመጠጥ በቀር የማይጠቀሙበት፣ ዝምታ ወርቅ ነው እያሉ ወርቅ የሚሸምቱበት ብዙ ናቸው፤ ከሕዝብ ጋር እየተጓዙ፣ በሕዝብ መሀል እየኖሩ የሕዝብ ጉዳይ (ፖሊቲካ) አይመለከተንም የሚሉ የማሰብ ችሎታቸውን ህልውና ይጠራጠሩ፤ የማሰብ ችሎታ ከሌለ የማወቅ አምሮት ወይም ምኞት የሚኖር አይመስለኝም፤ የማወቅ አምሮት በሌለበት የማሳወቅ አምሮት ጎልቶ ሲወጣና ሲደናበር ማየት በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ ፌስቡክ የሚባለው መድረክ የመደናበሪያ መድረክ እየሆነ ነው፡፡ የማሰብ ችሎታው የሌላቸው ሰዎች ከሁለት አንዱን መንገድ በመምረጥ፣ ወይም በሁለቱም መንገዶች በመጠቀም ይሳተፋሉ፡– የማያውቁትን ለማሳወቅ በመሞከርና በዘለፋ! የማያውቁትን ለማሳወቅ መሞከርና ዘለፋ የባሕርይ ግንኙነት አላቸው፤ አሁን እዚያ ውስጥ አንገባም፤ በተለያዩ መስኮች፣ በተለያዩ ጉዳዮች፣ በተለያዩ የእውቀት ጥበቦች በሚያሰራጩት ፍንጥቅጣቂ በአእምሮና በመንፈስ ለመበልጸግ በመጣር ፈንታ በአጉል ትዕቢትና ፉክክር፣ በማይጠቅም ዘለፋና ማስፈራራት የፌስቡክን መድረክ ማበላሸትና ማርከስ ወደኋላ ይጎትተናል እንጂ ወደፊት አያራምደንም፡፡ መሠረታዊ የማሰብ መነሳችን ሳንገነዘብ የማሰብ ትርምስምስ ውስጥ እንገባና መውጣት ያቅተናል፤ ለምሳሌ በእውቀትና በእውነት መሀከል ያለውን ልዩነት ሳንገነዘብ እምነትን ስንሞግት የራሳችንንም ሆነ የሌላውን ጊዜ እናጠፋለን፤ እውቀትን በሙግት ለማጣራት ሲመጡብን ደግሞ ቶሎ ወደእምነት እንዞራለን፤ አጉል መሽከርከር ውስጥ እንገባለን፤ እንዲያው በሆነ ባልሆነው፣ ባወቅነውም ሆነ ባላወቅነው የመጣልንን ሁሉ መዘርገፍ አዋቂ አያሰኝም፤ ጎበዝ አያሰኝም፤ ብልህ አያሰኝም፤ ግን ባለጌ ያሰኛል፤ ባለጌ ነጻነትን አያውቅም፤ ለባለጌ ስድነት ነጻነት ይመስለዋል፤ ነጻነት ባለቤቱ ያጠረው ገደብ ወይም ወሰን አለው፡፡

ፕሮፓጋንዳው ስብዓዊነት ይኑረው!!! ሰው እየሞተ ነው!! ቁጥሩን ቤቱ ይቁጠረው!!! ግርማ ሰይፉ -

_girma_siefu - Satenaw Newsበሀገራችን ያለው ድርቅ ክብደት ከ1977ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ የመንግሰት ሹም ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡ ልዩነቱ ግን አሁን መንግሰት ይህን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን የሚልው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አቅም ግን መሬት ላይ ወርዶ ስናየ ወኔ ብቻ ይመስላል፡፡ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ የፈረንጆቹን ደጅ እንዳይጠኑ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡

“ደርግ” በ1977 የነበረፈውን ድርቅ ለዓለም ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን የዚያን ጊዜ በነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት መነሻ በሁለቱ ጎራ በሚደረገው ፍልሚያ ግዳይ የሚጣልብት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ለዓለም ህብረተሰብ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት የሶሻሊስቱ ተከታይ በመሆኑ ይህ ጎራ ይህን ድጋፍ የሚያደርግበት አቅም የሌለው ሲሆን ይህን ለማድረግ አቅም ያላቸው ምዕራባዊያን ግን ውጤቱን በደንብ ሳናየው ድጋፍ ላለመስጠት መቁረጣቸው ለችግሩ ክብደት አንዱ እንደ ነበር ለመረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልግም፡፡ በተጨማሪ ለ1997 ድርቅ ተገቢው ምላሽ በምዕራባዊያን እንዳይሰጥ በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት በተለይ ህወሃት እና ሻቢያ የተጫወቱት ሚና ቀላል የማይባል ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ሆነን ስናየው ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ጥቅም እንዳዋሉት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የኢህአዴግ መንግሰት ከምዕራባዊያኑ ጋር ያለው ቅርበት ከደርግ እንደሚሻል ስለሚታመን በተጨማሪ ህውሃትና ሻቢያ በዛን ጊዜ የሰሩትን ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመስራት የሚችል ታጣቂ ሀይል ባለመኖሩ ችግሩን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሰት አቅሙ የከብቶቹን ህይወት ለመታደግ ለምን አልተጠቀመበትም? ካልቻለ ደግሞ ምዕራባዊያኑ ድጋፍ ለማድረግ ከፈለጉ አሁንስ ቢሆን ከብቶቹ ሳይሞቱ እንዲደርሱልን ለምን አልተደረገም? የሚለው ጥያቄ ለማንሳት አርብቶ አድር መሆን አይጠበቅብንም፡፡

ሁሉም የሚረዳው አንድ ሀገር በድርቅ መቼም ቢሆን ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ይህ በዓለም ላይ ተደጋጋሚ ክስተት እንደሆነ ማንም ያውቃል፡፡ ድርቅ ሲኖር ግን ይህን ድርቅ የሌላ ሶሰተኛ ሀገር ድጋፍ ሳይጠየቅ ለመፍታት አቅም መፍጠር መቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ስነ ምህዳር ከዚህ የተሻለ ማድረግ እና ለሌሎች መትረፍ ይገባት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሰማት ሳይሆን ሊተገበር የሚችል የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብሎ የሚያምን መንግሰት ያስፈልጋል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረግ ታንክ ሰራን በፍፁም በዚህ ወቅት ሊያኮራን የሚችል ስ አይደለም፡፡ አሁን የምንረዳው መንግሰት ችግሩን ሪፖርት አድርጊያለሁ ማለትን እንደመውጫ ቀዳዳ እየተጠቀመበት መሆኑን ነው፡፡

Thursday, November 5, 2015

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ነጻነት የሌለባት አገር ተብላለች – VOA

voa amharicጽዮን ግርማ / VOA

ፍሪደም ሃውስ (Freedom House) መቀመጫውን እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገና በመናገር ነጻነት ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡ይህ ተቋም መንግሥታት ለሕዝቦቻቸው የሚሠጡትን የኢንተርኔት ነጻነት አጥንቶ እያንዳንዱ ሀገር ያለበትን ደረጃ ‹‹Freedom on the net 2015 ›› በሚል ርዕስ ስር ሪፖርት አውጥቷል፡፡ በዚህ ሪፖርት ሰንጠረዥ‹‹ኢትዮጵያ ከቻይና፣ከሦሪያ እና ከኢራቅ ቀጥሎ ምንም ዓይነት የኢንተርኔት ነጻነት የሌለባት አገር ተብላለች፡፡

ዋሽንግተን ዲሲ—
ፍሪደም ሃውስ(Freedom House) የተሰኘው ተቋም “Freedom on the net 2015” የተሰኘው ይህ ሪፖርት በዛሬው ዕለት በቀረበበት ወቅት፤ሪፖርቱን ያዘጋጁት ባለሞያዎች፣የዩኒቨርስቲ መምሕራንንና ተመራማሪዎች፣የጎግል መስሪያ ቤት ባለሞያ፣ከመናገር እና ከመጻፍ ነጻነት ጋር የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች በአጠቃላይ ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚሠሩ ግለሰቦችና የድርጅት ተወካዮች ተገኝተው ሪፖርቱን አዳምጠዋል፡፡ ተወያይተዋል፡፡

ማንኛውም ሰው የኢንተርኔት የመረጃ መረብን ተጠቅሞ ያለምንም ቅድመ ምርመራ እና ችግር ሐሳቡን በነጻነት የማስተላለፍ መብት እንዳለው የሚጠቅሰው ይህ ሪፖርት በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥታት የሕዝቦቻቸውን የኢንተርኔት ነጻነት እያፈኑ፣አገልግሎቱንም እየዘጉ ከዛ ባለፈ ደግሞ እያሠሩ እንደሚገኙ ይጠቅሳል፡፡
voa amharic
አገራት ለሕዝቦቻቸው የሚሰጡትን ነጻነት በሦስት ቀለማት ከፍሎ ያስቀመጠው የሪፖርቱ አንድ አካል የኾነው አንድ ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ ከቻይና፣ከሦሪያ እና ከኢራቅ ቀጥሎ “የባሰ አፈና” ባለባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ ያስቀምጣታል፡፡ በሌላኛው የሪፖርቱ ክፍል ደግሞ “ኢትዮጵያ የኢንተርኔትም ኾነ የመናገርና መጻፍ ነጻነት ያለባት አገር አይደለችም” ይላታል፡፡voa amharic