
(በነገራችን ላይ ይህ ወግ፤ ከዘንድሮው ምርጫ ጋር በግርጌም ሆነ በራስጌ ኣይገናኝም ፡፡ ወጉ ስለጠበሳና ስለ ግጥም ነው፡፡በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ ስለ ጠበሳና ስለግጥም ማውጋትን እንደ ቅብጠት የምትቆጥሩ ኣርበኞች ከዚህ ተመለሱ፡፡)
ወደ ጨዋታው ስንመለስ፤መንግሥቱ ለማ ኮረዳዋ ከንፈር ላይ ከንፈሩን ለማስቀመጥ የሚያስችለውን የረጅምና ያጭር ጊዜ እቅድ ነደፈ፡፡ ሴትን በመማረክ ረገድ፤ በመንግሥቱ ለማ ጊዜ እና በኣባቱ በኣለቃ ለማ ዘመን መካከል ከባድ ልዩነት ኣለ፡፡በኣለቃ ለማ ዘመን ኣንዲት ሴት ከፈለግካት ጉልበትክን ተጠቅመህ ትማርካታለህ፡፡ መፍትሄው ኣበባ ሳይሆን የወይራ ሽመል ማበርከት ነበር፡፡ በፈረስህ ኣባረህ እንሥራዋን ጀርባዋ ላይ ሰብረህ ወደ ጫጉላ ይዘሃት ትዘምታለህ፡፡
መንግሥቱ ለማ ላቅመ- ኣምሮት በደረሰበት ዘመን ላይ የነበረው ስልጣኔ ሴቶችን ከተጠቂነት ወደ ኣጥቂነት ኣሸጋግሯቸዋል፡፡ ቆነጃጅትን “የሚታዩ እንጂ የማይበሉ ፍሬዎች” ኣድርጓቸዋል ፡፡ በዚያ ዘመን ህጉን ሳትጋፋ ልጂቷንም ሳታስከፋ ኣንዲት ቆንጆ ሴት ከንፈር ላይ ለመድረስ ረጅምና መራራ ትግል ማለፍ ይጠበቅሃል፡፡
“የደጋ ማርና፤ የቆንጆ ልጅ ከንፈር
ወድቀው ካልተነሡ፤ በዋዛ ኣይደፈር”
እንዲል ገጣሚው ሙሉጌታ ተስፋየ፤ በኣበበ ተካ ዜማ፡፡
“የደጋ ማርና፤ የቆንጆ ልጅ ከንፈር
ወድቀው ካልተነሡ፤ በዋዛ ኣይደፈር”
እንዲል ገጣሚው ሙሉጌታ ተስፋየ፤ በኣበበ ተካ ዜማ፡፡
ከእለታት ኣንድ ቀን መንግሥቱ ለማ የከጀላትን ልጅ እንደምንም ኣግባብቶ ሲኒማ ጋበዛት፡፡ሲኒማው እንዳከተመ፤ ቤቷ ድረስ ሸኝቷት በር ላይ ካደረሳት በኋላ በሲኒማው ውስጥ ያሉት ፈረንጆች እንደሚያደርጉት በ“ጉድ ባይ ኪስ” ሊያቀልጣት ከንፈሩን ከሰገባው መዘዝ ኣደረገ፡፡ከዚያ በኋላ ባካባቢው የተሰማው እምጵዋዋዋዋዋ የሚል ሳይሆን ጦዋዋዋዋዋዋ የሚል ድምጽ ነው፡፡የዚያን ቀን ምሽት በመንጌ ፊት ላይ ያረፈው ጥፊ ለኣማርኛ ስነግጥም ትልቅ ኣስተዋጽኦ ኣድርጓል፡፡
በጠራ ጨረቃ
በጠራ ጨረቃ፤ በእኩለ ሌሊት
ዓይኖቿ እያበሩ፤ እንደ ከዋክብት
ሳማት ሳማት ኣሉት፤ እቀፍ እቀፋት
ኣላወላወለም፤ ወጣቱ ታዘዘ
ወገቧን ኣንገቷን ፤በእጅና እጁ ያዘ
ምንም እንኳ ጡቷ፤ እንደሾህ ቢዋጋ
ጣቷ በመሆኑ፤ የጉማሬ ኣለንጋ
ጆሮ ግንዱን ሰማው ፤በጥፊ ሲናጋ
በጠራ ጨረቃ፤ በእኩለሌሊት
ዋ ጀማሪ መሆን፤ ዋ ተማሪነት
(መንግስቱ ለማ)
በጠራ ጨረቃ፤ በእኩለ ሌሊት
ዓይኖቿ እያበሩ፤ እንደ ከዋክብት
ሳማት ሳማት ኣሉት፤ እቀፍ እቀፋት
ኣላወላወለም፤ ወጣቱ ታዘዘ
ወገቧን ኣንገቷን ፤በእጅና እጁ ያዘ
ምንም እንኳ ጡቷ፤ እንደሾህ ቢዋጋ
ጣቷ በመሆኑ፤ የጉማሬ ኣለንጋ
ጆሮ ግንዱን ሰማው ፤በጥፊ ሲናጋ
በጠራ ጨረቃ፤ በእኩለሌሊት
ዋ ጀማሪ መሆን፤ ዋ ተማሪነት
(መንግስቱ ለማ)
- በምትመለከቱት ፎቶ ውስጥ የግጥሙ ቀስቃሽ የሆነችው ሜሪ ታደሰ ትታያለች፡፡ ፎቶ ግራፉን ባየሁ ቁጥር ኣይኔ ኣስቀድሞ የሚያርፈው መዳፏ ላይ ነው፡፡“ጆሮ ግንዱን ሰማው በጥፊ ሲናጋ”የሚለው መስመር ግነት ኣለመሆኑን ለመረዳት የእጇን መዳፍ ግዙፍነት ማየት ይበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment