OPPOSITION PARTIES WEBSITES

ETHIO NEWS & VIEWS

RADIO & TV

Tuesday, May 19, 2015

በርግጥ ኢትዮጵያ እንዲህ የሚያኮሩ አባቶች አሏት – የሚሊዮኖች ድምጽ

medrekበጣም ልቤን የመሰጠው አንድ ምስክርነት አነብብኩ። አንዲት እህት ስለ አባቷ የጻፈችዉን። ዳኛ የነበሩ ጊዜ በጥቅምና በጉቦ ፍርድን እንዲአይዛቡ እርሳቸዉን ለመደለል ሲምከር የመለሱት መልስ ይች እህት ጠቅሳለች። “ለገንዘብ ስል ፍትህን አላዛባም። ልጆቼን ሽሮ እያበላሁ ንፁህ ህሊናን አወርሳቸዋለሁ” ነበር ያሉት ይች እህት እስከድዳር አለሙ ናት። የርዮት አለሙ እህት። መነበበ ያለበት ምስክርነቷ እንሆ፡
“ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ምሳሌ 22÷6
ይህን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ሳይ ሁሌም ወደ አይምሮዬ የሚመጡት አባቴ አቶ አለሙ ጎቤቦ እና እህቴ ርዕዮት አለሙ ናቸው፤ ምክንያቱ ደግሞ ለርዕዮት የመልካም ስብዕና ባለቤት መሆን አባቴ በመልካም መንገድ እንዴት እንደመራት ያስታዉሰኛልና ነው።
ዛሬ ስለ አባታችን እና ስለ ልጅነት ትዝታዬ ትንሽ ልነግራችሁ አሰብኩና ይህቺን ማስታወሻ ፃፍኩ።
በአንድ ወቅት ጋሽዬ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እያለ በቤታችን ውስጥ የተከሰተዉ ነገር በልጅነት አይምሮዬ ታትሞ ቀረ፡፡ ይህም ክስተት እስከዛሬ ድረስ ባስታወስኩት ቁጥር በአባቴ እንድኮራ ያደርገኛል፡፡
ምን ሆነ መሰላቹ ? ቀኑ እሁድ ስለነበር ጋሽዬ እቤት ነበር የዋለው፤ እሱ እቤት ሲሆን ቤቱ ራሱ የተለየ ድባብ ስላለው ሁላችንም እሁድን እንናፍቃት ነበር፡፡ የዛን እለት ሁለት እንግዶች ወደቤታችን መጡ ።ጋሼ እና እቴቴ ግራ ተጋቡ እንግዶቹን ስላላዉቋቸዉ፡፡ ቁጭ እንዲሉ ሲጋብዟቸዉ ጋሼን ለብቻው ማናገር እንደሚፈልጉ ገለፁለት ። ተያይዘው ወደ በረንዳ ወጡ፤ ብዙም ሳይቆዩ ጋሽዬ ባልተለመደ ሁኔታ ድምፁን ከፍ አርጎ መናገር ጀመረ ። “እኔ አለሙ ነኝ በእናንተ መደለያ ፍርድ የማዛባዉ? አሰለፈች (እቴቴን) ነይ እነዚን ጉዶች ስሚ። ጉቦ ይዘው ተቀበለን ሲሉ” ። ሰዎቹ ጋሼን ለማረጋጋት ሲጥሩ እቴቴም ወጥታ ከጋሼ በሚበልጥ ድምጽ “ማን ጋር የመጣችሁ መሰላቹህ ? አለሙ እኮ ነው. . . ” አለቻቸው። አቤት ውርጅብኝ! ባልና ሚስቱ ለሁለት ሰዎቹን የሚገቡበት አሳጧቸዉ፡፡
ነገሩ በሰአቱ ስላልገባኝ እህቴን (ርዕዮትን) ምን እንደተፈጠረ ስጠይቃት “ጋሽዬን ዋሽ እያሉት ነው” አለችኝ፤ እነዛ ሰዎች ለእነሱ እምቢ ሲል በተለያዩ ሰዎች ቤታችንን ማንኳኳት ቀጠሉ። ጋሽዬም በእምቢታዉ ፀና፤ የመጨረሻ ቀን የተናገራት ንግግሩ ግን ለህይወቴ ስንቅ ሆነችን “ለገንዘብ ስል ፍትህን አላዛባም። ልጆቼን ሽሮ እያበላሁ ንፁህ ህሊናን አወርሳቸዋለሁ”
ይህ ከሆነ አመታት ቢያልፉም የጋሼ አቋም ግን አልተለወጠም። ዛሬም “ፍትህን” ይላል። ዛሬም “እዉነትን” ይላል፡፡ ለዚህም ነዉ ከላይ ያቺን ጥቅስን ያስታወስኳት፤ ንፁህ ህሊናን ለልጁ ለርዕዮት አወረሳት እሷም ከዛ ፈቀቅ አላላችም፡፡ መልካም አባት!
ዛሬም ፍትህን መናፈቁን አላቆመም። ለሀገሩ የበኩሉን ለማበርከት በመጪው እሁድ በሚደረገው ምርጫ ላይ የወረዳ4 የመድረክ እጩ ሆኖ ቀርቧል። ያለፈው የ2002 ምርጫ ላይ ተሳታፊ ሆኖ አለመሳካቱ ካሁኑ ምርጫ አላስቀረዉም። እንደውም በበለጠ ሃይል እና ብቃት እንዲሆን አረገው እንጂ (በነገራችን ላይ በ2002 ምርጫ ላይ ርዕዮትም እኔም የአባታችን ታዛቢ ነበርን አሁን ግን ርዕዮት. . . )
ርዕዮት በመፅሐፏ ምስጋና ላይ ለጋሽዬ ይህን ነበር ያለችው “የምረቃዬ ዕለት የተናገርከው ትዝ ይልሀል?” ርዕዮት የስጋ ልጄ ብቻ ሳትሆን የባህሪ ልጄም ናት፡፡” ነበር ያልከው፡፡ “አዎን! ከምንም በላይ ስለ እውነት መኖርን አስተምረኸኛልና አመሰግንሀለሁ”
ጋሽዬ ከምንም የሚበልጠውን እውነትን አውርሰኸናልና ክብር ይገባሃል፡፡ ሁሌም እወድሀለሁ። ባለ ንፁህ ህሊናው አባታችን!!!!

No comments:

Post a Comment