OPPOSITION PARTIES WEBSITES

ETHIO NEWS & VIEWS

RADIO & TV

Monday, April 27, 2015

አይኤስን ለማውገዝ በተጠራው ሠልፍ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረው ግጭት በርካቶች ታስረው ተፈቱ

9c43080680d37654411f246864041403_Lሠልፉን በዋነኝነት በጥብጠዋል የተባሉ ተለይተው ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል
-ሰማያዊ ፓርቲ መንግሥት ስሜን እያጠፋ ነው አለ
በሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመውን የአይኤስ የሽብር ቡድን ድርጊት ለማውገዝ፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በወጡ የሠልፍ ታዳሚዎችና በፖሊሶች መካከል በተፈጠረው
ግጭት ከ900 በላይ ተሳታፊዎች ታስረው ተፈቱ፡፡ ሠልፉን በዋናነት በመበጥበጥ በሠልፈኞችና በፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተለይተው የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ በፍርድ ቤት ተጠይቆባቸዋል፡፡
አይኤስን የማውገዙ ሥነ ሥርዓት ሊጠናቀቅ ሲል ጩኸት፣ ስድብና ድንጋይ ውርወራ ሲጀመር የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በወሰዱት ዕርምጃ በዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ቢሆንም፣ ማምሻውን እየተለዩ በሠልፉ ውስጥ ብቻ በመገኘታቸው ብቻ አብረው የታሰሩ ናቸው የተባሉ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ብጥብጡ እንደተጀመረ ድንጋይ ውርወራ ስለነበር የሠልፉ ተሳታፊዎች ቁጥራቸው ባይታወቅም የተፈነከቱ፣ እግራቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ፣ የተወሰኑ ወጣቶች ደግሞ ራሳቸውን ስተው የወደቁ እንደነበሩና ፖሊሶችም በሩጫ የደረሱባቸውን በዱላ ሲዠልጡ እንደነበር በግርግሩ ወቅት ለማየት ተችሏል፡፡
በተለይ በአይኤስ የሽብር ቡድን አባላት አሰቃቂ ግድያ ከተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያን መካከል የሁለቱን ወጣቶች፣ የወጣት ኢያሱ ይኩኖአምላክና የወጣት ባልቻ በለጠን ስም እየጠሩ ከፍተኛ ተቃውሞአቸውን በመንግሥት ላይ ሲያሰሙ የነበሩ ወጣቶች፣ ተቃውሞአቸው ሙሉ በሙሉ በመንግሥትና ፊት ለፊታቸው በሚያዩዋቸው የፖሊስ አባላት ላይ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በድንጋይ ውርወራ የተጀመረው ግጭት አስፈሪ ነበር፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የሠልፉ ተሳታፊዎች በትንሿ ስታዲየም፣ በቂርቆስ፣ በለገሀር፣ በአምስተኛ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአራዳ፣ በኮተቤ፣ በላምበረትና በሌሎችም ቦታዎች መታሰራቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ሪፖርተር የታሳሪዎቹን ቁጥር፣ ጉዳት የደረሰባቸውን የተሳታፊዎች ብዛትና የተጎዱ የፖሊስ አባላት፣ እንዲሁም በአንዳንድ ወገኖች እየተነገረ የሚገኘውን የአንድ ሠልፈኛ ‹‹ሞት›› የተባለውን ለማጣራት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የፖሊስ አባላት ስለሁኔታው አስረድተዋል፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያውያን (በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ ያሉትን) ልብ የነካ ሐዘን ተከስቶ፣ ሁሉም ቁጭቱንና ሐዘኑን በሚገልጽበት ቀን ወደሌላ ብጥብጥ ማምራቱ እንዳሳዘናቸው የገለጹት የፖሊስ አባላቱ፣ በዕለቱ በርካታ ሰዎች ብጥብጡ ውስጥ ሲሳተፉ የተያዙ ቢሆንም፣ እየተጣራ በዕለቱ አብዛኛዎቹ መፈታታቸውን አስረድተዋል፡፡ ቁጥራቸው ከ900 በላይ የሚሆኑ በየክፍለ ከተማቸው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የተበተኑ መሆናቸውን፣ ፍርድ ቤት ቀርበውም ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አባላቱ ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ በሠልፉ የተሳፉና የተጎዱ ቢኖሩም፣ በአንድ ሰው ላይ ብቻ ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በቀር ቀሪዎቹ ከሚወረወር ድንጋይ ለማምለጥ ሲሯሯጡ እርስ በርሳቸው ተጠላልፈው በመውደቅ የተጎዱ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ የሞተ ሰው ግን አለመኖሩን አባላቱ ተናግረው፣ አስፈላጊ ከሆነም የሚመለከተው ተቋም [ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል] ሊጠየቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ ከተሳታፊዎቹ በተወረወረ ድንጋይ ሰባት የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ መሆናቸውን፣ ሌሎችም ሲቪል የለበሱ የፖሊስ አባላትም ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡
ለብጥብጡ መነሳት ወይም ሆን ብለው መንግሥትና ሕዝብ እንዲጋጭ በር ከፋች መሆናቸው ተረጋግጦባቸዋል የተባሉ ከ16 በላይ ተጠርጣሪዎች ተለይተው፣ ለብቻቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ አንዷ በቅርቡ ከካናዳ የመጣች መሆኗም ታውቋል፡፡
በዋና ተጠርጣሪነት የታሰሩትም ሆነ በየክፍላተ ከተማው ተበትነው የታሰሩት ላይ፣ ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቦ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ቢሆንም፣ በየክፍላተ ከተማው ያሉት አብዛኛዎቹ መፈታታቸው ተጠቁሟል፡፡
በዕለቱ በሠልፈኞቹና በፖሊስ መካከል የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በሰጡት መግለጫ፣ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆን ብለውና ሲዘጋጁ ከርመው ብጥብጡን የሚያስነሱ ጥቂት ሰዎችን ማዘጋጀታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የአቶ ሬድዋንን መግለጫ ተከትሎ ሰማያዊ ፓርቲም በዕለቱ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት የጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ በመደገፍ አባላቱ በሠልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሶ፣ ጥሪውን መሠረት በማድረግ አመራሮቹና አባላቱ ገና ወደ መስቀል አደባባይ በመሄድ ላይ እያሉና በሠልፉ ላይም ከተገኙት ውስጥ እየተለቀሙ መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በርካታ ዜጎች በቁጭትና በሐዘን የተገኙ ተሳታፊዎች ተቃውሞአቸውን ‹‹ንግግር በሚያደርጉ›› ሰዎች ላይ በመግለጻቸው፣ መንግሥት ፕሮግራሙን በችኮላ እንዲጠናቀቅ ማድረጉን የገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ለሕዝብ ተቃውሞና ቁጣ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የማይወደው መንግሥት፣ በዜጎች ላይ የወሰደው ዕርምጃ እንዳሳዘነውና እንደሚያወግዘውም አስረድቷል፡፡
‹‹መንግሥት ሠልፍ ተጠርቶ በወጣው ሕዝብ ላይ የወሰደውን ዕርምጃ ለመካድና የሕዝብን ከፍተኛ ተቃውሞ ለመደበቅ፣ እንዲሁም የሕዝብን ቁጣና ሐዘንን የሰማያዊ ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ እንደሆነ አድርጎ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መግለጫ ማውጣቱ አሳዛኝ ነው፤›› ብሏል፡፡
‹‹መንግሥት በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚያሳየውን ቸልተኝነት በተቃወሙ ዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ ዕርምጃ ሳያንስ፣ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር አዛምዶ ተቃውሞአቸውን ማጠልሸት ትክክል እንዳልሆነና ከመንግሥት የማይጠበቅ ስህተት ነው፤›› በማለት ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር እንዲካሄድና የአመፅና የጦርነት አዙሪት እንዲከስም፣ ጭቆናን ተቋቁሞ የሚያደርገውን ትግል ለማኮላሸት መንግሥት መሞከሩ፣ የከፋ አደጋ እንዳለው ለማስገንዘብ እንደሚወድ ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው አካቷል፡፡
የአይኤስ የሽብር ቡድን ድርጊትን ለማውገዝ የተወካዮች ምክር ቤት በጠራው ሠልፍ ላይ ለመሳተፍ ሲወጡ፣ በሠልፉ ውስጥ እያሉና የታሰሩትን ሊጠይቁ ሲሄዱ የታሰሩ አባላቱ የድርጅት ጉዳይ አባል ወይንሸት ሞላ፣ የ2007 አገራዊ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ተወዳዳሪ ጠና ይታየው፣ የፓርቲው አባል ኤርሚያስ ሥዩም፣ የቂርቆስና የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተባባሪዎች ማስተዋል ፍቃዱና ዳንኤል ተስፋዬ፣ የአዲስ አበባ ምርጫ ጉዳይ ኮሚቴ ሕዝብ ግንኙነት ቴዎድሮስ አስፋው፣ በ2007 ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተወዳዳሪ እስክንድር ጥላሁንና ሌላው የተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ ይድነቃቸው አዲስ እንደታሰሩበት አስታውቋል፡፡ በሠልፈኞቹ ላይ እስር፣ እንግልትና አሰቃቂ ድብደባ የፈጸሙና ትዕዛዝ ያስተላለፉ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ እንደሚጠይቅም ሰማያዊ ፓርቲ ገልጿል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment