OPPOSITION PARTIES WEBSITES

ETHIO NEWS & VIEWS

RADIO & TV

Friday, March 20, 2015

ዳንኤል ክብረትና ሌላው የወያኔያዊ ተግባሩ መገለጫ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋውለዛሬ ቀጠሮ አለን አይደል? “የሀገርና የቤተክርስቲያን ታሪክ ጠላት ስውሩ ተኩላ ዳንኤል ክብረት!” በሚለው ጽሑፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የዳንኤልን ወያኔነት እንድረዳ ያደረገኝ ከላይፍ መጽሔት ጋር ቅጽ 7 ቁጥር 102 መጋቢት 2005ዓ.ም. ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ያነበብኩ ጊዜ ነው፡፡ ይኔንን ጉዳይ በተመለከተ በሚቀጥለው ጊዜ ይዠላቹህ እቀርባለሁ ብየ ነበርና፡፡ ከዚህ በፊት ግን አንዳንድ ነገሮችን እንዳነሣ ፍቀዱልኝ? ጥቂት የማትባሉ እኅት ወንድሞች በባለፈው ጽሑፍ ውስጥ በነበሩት የተግሳጽና የዘለፋ ቃላት እንዳልተደሰታቹህ ከአስተያየታቹህ ተረድቻለሁ፡፡ ትክክልም ናቹህ፡፡ ይቅርታም ልጠይቃቹህ እወዳለሁ፡፡ ምን ላድርግ ብላቹህ ነው? በሀገሬ በቤተክርስቲያንና በዚህ ውድ ሕዝብ እንዲህ ዓይነት ሸፍጦች ሲፈጸሙ አልችልም፡፡ እንዲህ ተናግሬም በወጣልኝ ምንኛ በታደልኩ ነበር፡፡ ዘለፋው ይገርማቹሀል እንዴ! እውነቴን ነው የምላቹህ ፈንጅ በእጀ ቢኖር አንድ ሰው የማስተርፍ አይመስለኝም፡፡ በግል ጉዳየ እኮ ሰላማዊና ቻይ ነኝ በእነዚህ በሦስቱ ሲመጡብኝ ነው የማልችለውና ደመ ፍሉ የሚያደርገኝ፡፡ ይሄው በዚህ ችግር ላይ መታረም እቅቶች እዳለሁ አለሁ፡፡ ይሄንን ችግር እንዲያርቅልኝ ጸልየበታለሁ ሁሉ፡፡ እስኪ እባካቹህ እናንተም በጸሎታቹህ አስቡኝ? ለንስሐ እንዲያበቃኝም እንደዚያው፡፡ ለነገሩ እኮ ግን እስኪ ከጠቀስኳቸው የተግሳጽና የዘለፋ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች ያልተገሰጹበትንና ያልተጠቀሰውን አንድ የዘለፋ ቃል እንኳን ልታወጡልኝ ትችላላቹህ? እና ታዲያ የኔ ስሕተት ምኑ ላይ ነው? ቃሉ እንደሚፈቅድልኝ አታውቁም? “ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገስክና እያስተማርክ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” 2ኛ ጢሞ. 4፤2 ተቆጣም ይላል ባይሆን በቁጣህ ግን ፀሐይ አይግባ ይላል እንጅ፡፡
ዋናው እኔ ልወስደው የሚገባኝ ጥንቃቄ ይሄ እየገሠጽኩት እየዘለፍኩት ያለሁት ሰው በእርግጥ እያልኩት እንዳለሁት ሊያዘልፍ ሊያስገሥጽ በሚገባ ግብር ላይ ተገኝቷል ወይ? የሚለው ነገር ነው እንጅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥፊዎች የተገሠጹበትን ቃል ለሱ መጠቀሜ አይደለም፡፡ ዳንኤል በዚህ ከባድ ጥፋትና ድፍረት ለመገኘቱ ደግሞ መረጃዎችን እየጠቀስኩ እንዳረጋገጥኩ ሁሉም የአንባቢ ዓይነት አንብቦ ሊረዳው በሚችል አገላለጽ ገልጨ መጻፌን እናንተው እራሳቹህ ምስክሮች ናቹህ፡፡ ዳንኤል በፊት በሠራቸው ጥሩ ጥሩ ሥራዎቹ ያደረባቹህ አክብሮትና ፍቅር ይዟቹህ ነው እንጅ አሁን ማን ይሙትና በግልጽና ማንንም ሊገባ በሚችል አማርኛ መረጃ እየተጠቀሰ የተጻፈው ሳይገባቹህ ቀርቶ ነው በቁጣና በኃይለ ቃል ስለ ዳንኤል ተቆርቁራቹህ እኔን የስድብ መዓት ያሸከማቹህኝ? የሰደባቹህኝን ሰዎች ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቃቹህ ከሀገርና ከቤተክርስቲያን ይልቅ ዳንኤል በልጦባቹህ ነው ይፋዊ መረጃዎች ተጠቅሰው ሥራው ተገልጾላቹህ እያለ አንሰማም ዐናይም ብላቹህ እንደዚያ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትሉ የነበረው? በእውነት ስለእናንተ እኔ አፈርኩላቹህ፡፡ ልታደርጉ የሚገባቹህ የነበረው የተባለውን ይዛቹህ እውነት ነው ወይስ ሐሰት? በማለት የራሳቹህን ማጣራት አድርጋቹህ ስለሀገርና ቤተክርስቲያን እንዲሁም ሕዝቧ ሲባል እውነቱ ወዳለበት መቆም ይኖርባቹሀል እንጅ “ወንድሜን የበላ ጅብ እኔንም ይብላኝ” አይባልም፡፡ ይሄ በሳል ውሳኔ አይደለም፡፡ የእውነት ተከታይ ሁኑ እንጅ የሰው ተከታይ አትሁኑ፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት ይህች ቤተክርስቲያን ባለፉት ጥቂት ዐሥርት ዓመታት ስንት መንጋ አጥታለች መሰላቹህ! እውነትን ሳይሆን ሰው ስለተከተሉ ያ ሰው ገደል ሲገባ አብረው ገደል የገቡ ስንት መንጋ አለ መሰላቹህ! ያንን ሰው ልታደምጡት የሚገባቹህ ከእውነት ጋራ እስካለ ጊዜ ድረስ ብቻ እንጅ በጥቅምም በትዕቢትም በአመለካከት ችግርም በምንም ተጠልፎ ወድቆ እያያቹህትም መሆን የለበትም፡፡ ይሄ ከዋህነትም አልፎ ጅልነት ነው እንዲህ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ፡፡
ገና “በአይሁዶች መርዘኛ ጥርስ የገባች ሀገር ኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ ስለ ዳንኤል ልጽፍ እንደሆነ ከጠቆምኩ ጊዜ ጀምሮ ነበር ጽሑፉን እንዳልለቀው በርካታ መስመ እግዚአብሔርና በወላዲተ አምላክ ስም የሚማጸኑ መልእክቶች የደረሱኝ፡፡ “ታዋቂ ሰውን በመተቸት እውቅና ለማግኘት ነው” ያሉም አሉ ስለ ጌቶቹ ስለ አባ ጳውሎስ ስለ አባ ማትያስ ስለ አቶ መለስ ስለ አቶ ኢሳይያስ ስጽፍ ዕውቅና ለማግኘት ነው ያልተባልኩት ስለሎሌያቸው ስጽፍ ዕውቅና ለማግኘት ነው መባለ አስቆኛል፡፡ ስለ ዳንኤል የጻፍኩት ታዋቂ ስለሆነ ሳይሆን የሠራው ስሕተት በፍጹም የሚታለፍ ቸል የሚባል ባለመሆኑ ነው፡፡ ባጋጣሚ ዳንኤል ሆነ እንጅ አንድ ሌላ ማንኛውም ሰው ቢሆንም እንኳን ይሄ ጽሑፍ መጻፉ የሚቀር አይሆንም ነበር፡፡ የተቃወመ እንደመኖሩ ሁሉ የዛኑ ያህል ደግሞ ስንቱ ያርበት እንደነበር ከደረሱኝ መልዕክቶች ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ጽሑፉ ከወጣ በኋላ ደግሞ ቀጣዩ ይሄኛው እንዳይወጣ አሁንም ከወቀሳ ጋር ተመሳሳይ ልመና ነበር ይላክ የነበረው፡፡ ሰዎቹ ምን እያደረኩ እንደሆነ ፈጽሞ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ ይሄ የግል አንባጓሮ ቢሆን ስለ ጠሩት የእግዚአብሔር ስም ክብርና ስለ ቤተክርስቲያን ጥቅም ብየ እንዳሉት መተው ተገቢ በሆነ ነበር፡፡ ይሄ ጉዳይ ግን የቤተክርስቲያን ጉዳይ ነው፤ የሀገርና የሕዝብ ታሪክና ማንነት ጉዳይ ነው ስለዚህ ጉዳይ ተብሎ እናት አባቶቻችን ስንትና ስንት መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እንዲህ ሆኖ እያለ ይህ ጉዳይ እንዳይገለጥ በስመ እግዚአብሔር መገዘትና መማጸን ተገቢ ነው? ምን እያደረጉ እንዳሉስ ያውቁታል? ይሄ “ወፈ ገዝት” ይባላል ግዝቱም አይሠራም የእግዚአብሔርን የአምላክን ስም እንዲህ ለማይገባ ነገር በከንቱ መጥራት ያስጠይቃልና እንጠንቀቅ፡፡
ዓላማየ ምን ሆነና? ቤተክርስቲያን የምትጎዳው በጉያዋ ተወሽቆ የሚያደማት የሚጎዳት ታሪኳን ቅዱሳት መጻሕፍቷን የሚያጠፋፋባት የሚቆነጻጽልባት ተኩላ ሳይታወቅ ተደብቆ ሲያጠፋት ሲያቆስላት ደም ስሯን ሲቆርጣት ነው ወይስ ሲጋለጥ? እንዴት እንደሚያስቡ አልገባኝም፡፡ ጉዳዩን በግል መጨረስ ሳላስብበትና ሳልሞክር ቀርቸ አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ እንደሚያስቡት ዳንኤል “አዎ አጥፍቻለው” ብሎ ከዚህ ተግባሩ የሚመለስ የጻፈውንም ጽሑፍ የተሳሳተ መሆኑን የሚገልጽ ይመስላቹሀል? በእውነት የዋሀን ናቹህ፡፡ ዳንኤል ምክር የሚሰማ ጆሮ አስተያየት የሚቀበል ልብ የለውም፡፡ አንዴ ምን እንዳደረገ ልንገራቹህ? “አራቱ ኃያላን” የሚለውን መጽሐፍ እንዳስመረቀ ወዲያው አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በአንድ የቤተክርስቲያን ድረ ገጽ ላይ መጽሐፉን የገመገመበትን አተያይ አስቀመጠ እኔም በአስተያየት መስኩ ላይ አስተያየቴን አስቀመጥኩ ለኔ አስተያየት ሁለት አንባቢያን በተቃውሞ አስተያየት ሰጡ እኔም ለነሱ መልስ እንደሰጠሁ የበፊቱን አስተያየቴን ጨምረው ከገጹ አጠፉት፡፡ ከዚያ ብሎግ ይሄንን እርምጃ አልጠበኩም ነበር ብሎጉ የኔንም ጽሑፎች ይለጥፍ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን ከእኔ ይልቅ ዳንኤል ስለቀረባቸው እንዲያተፉት ሲነግራቸው አላቅማሙም፡፡ ያንኑ አስተያየት ከራሱ ከዳንኤል ገጽ ላይ ላሠፍረው ፈለኩና ገብቸ ላሠፍረው ስሞክር ለካ አግዶኝ (ብሎክ አድርጎኝ) ኖሮ አስተያየቴን ማስፈር እንዳልችል አደረገኝ፡፡ አስተያየቱ እንዲህ ይል ነበር፡-
ጥሩ ትዝብት ነው ብርሃኑ፡፡ ዲ/ን ዳንኤል እየሠራ ያለው ሥራ በእውነት እጅግ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስከው ይህ ሥራ ሊሠራ የሚገባው በቤተክርስቲያኗ ቢሆንም የቤተክርስቲያኗ ወቅታዊ ተቋማዊ የአደረጃጀትና አቋም ወይም መዋቅር የወቅቱ ፖለቲካዊ ጥቅም የተጫነው በመሆኑ ይሄንንና መሰል ሥራ ለመሥራት የሚታሰብ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ይሄንን ክፍተት ከመሙላት አንጻር የአቅም ውስንነቱ የሚያሳድረው የራሱ የሆነ ችግር ቢኖርም ቅሉ ዲ/ን ዳንኤልን ጨምሮ የአንዳንድ ወገኖች ጥረት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ዋነኛ ዓለማው የሚመስለኝ በዚህ ዘመን ያሉቱ አባቶች መንፈሳዊና ግብረገባዊ ብቃት ከቀድሞዎቹ አባቶቻችን ጋራ ሲነጻጸር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየትና የቀደሙቱ አባቶቻችንን የዓላማ ጽናት በአርዓነት እዲወሰድ ለማድረግ የሚሞክር ነው ወይም መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ የቀደሙትን አባቶቻችንን አርዓያ አድርጎ እንደነሱ ሁሉ ክርስቲያናዊ ተአምኖ እንደሚጠይቀውና ግድ እንደሚለው በድፍረትና በጽናት መጋደል በአባቶች ብቻ ሳይወሰን ሁሉም ክርስቲያን ሊያደርገውና ሊኖርበት የሚገባ ሕይዎት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የዚህ መጽሐፍ እም…. ምን እንደምል አላውቅም በእርግጥ ማስታወቂያዎች ላይ ደራሲ ተብሎ ተጽፎ ዓይቻለሁ መጽሐፉም ላይ እንደዛ የተባለ ይመስለኛል ነገር ግን ስሕተት ነው፡፡ ደራሲ የሚባለው ወጥ የድርሰት ጽሑፍ ሲሆን ነው፡፡ መጽሐፉ አስቀድሞ የነበረ ከሆነና ያም መጽሐፍ በሌላ ቋንቋ የነበረ ሆኖ የተመለሰ ከሆነ “ተርጓሚ” የሚለውን ቃል እንጠቀማለን፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የዲ/ን ዳንኤል ሚና በዚህ መጽሐፍ ላይ መጻሕፍቱን ግእዝ በሚያውቁ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አስተርጉሞ በመሆኑ ተርጓሚም ማለት አንችልም፡፡ ወደ ቅኔ ቤት ወርዶ ግእዝን ጠንቅቆ ዐውቆ መተርጎምና በግል ጥረት በመጠኑ አንዳንድ ቃላትን አውቆ ለመረዳት ያህል ግእዝን ለማወቅ መሞከር የተራራቁ በመሆናቸውና መጻሕፍትን ተርጉሞ በማቅረብ ሥራ ላይ ከባድ የጥራት ችግር ስለሚፈጥሩ፡፡ ነገር ግን አዘጋጅና አሳታሚ የሚለውን ቃል መጠቀም የምንችል ይመስለኛል፡፡ ይህ ስሕተት በዚህ መጽሐፍ ብቻ የታየ አይደለም፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ከዚህ ቀደም ባሳተማቸው መጻሕፍትም ተስተውሏል ቀደም ሲል የነበሩትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ አማርኛ አስተርጉሞ ስላሳተማቸው የደራሲ ሚና ሳይኖረው “ደራሲ” ተብሎ ተጽፎባቸው ተመልክቻለሁ፡፡ እሱም አንድ ሬዲዮ ላይ እንግዳ ሆኖ ቀርቦ ጋዜጠኛው 19 መጻሕፍት ደርሰሀል ልክ ነኝ? ብሎ ሲጠይቀው ትክክል ነህ ብሎ ሲመልስ አድምጨዋለሁ፡፡ ይሄ ዳንኤልን ትንሽ ትዝብት ላይ የሚጥለው ስለሆነ እርማት ቢወስድበት መልካም ነው፡፡
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ይህ መጽሐፍ ሌላ ዓላማ የያዘ ካልሆነና በዚህ ወቅት ያሉ አባቶቻችንን ምእመናንንም የነዚያን ቆራጦች አባቶቻችንን አርዓያነት እንድንጋራ እንድንወስድ ለማድረግ ከሆነ ዓላማው መልካምና የሚደገፍ ይሆን ነበር ነገር ግን ዲ/ን ዳንኤል ለአባቶች ያነሣውን ጥያቄ ለራሱም የሚነሣ ከመሆኑና እሱ አራሱም ከዚህ ወቀሳ ነጻ ባለመሆኑ ማለትም በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሱት አባቶቻችን ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ በድፍረትና በግልጽ ስለ እውነት ስለፍትሕ መጋፈጥ ጨርሶ የማይወድ የማይፈልግ እራሱን እጅግ ለትዝብት በሚዳርግ ኢክርስቲያናዊ ብልጠት የተሞላበት አኪያሔድ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ አንባቢያን ከዚህ አኳያ ተመልክተውት የመጽሐፉ ፋይዳ ካልደበዘዘ በስተቀር መጽሐፉ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ መለስ ዲ/ን ዳንኤል እንደዚያ ደክሞ ለንባብ ስላበቃው እጅግ የሚያስመሰግነው ነው ያበርታህ ልለው እወዳለሁ፡፡ ወደፊት መጽሐፉን ገዝቸ ካነበብኩት በኋላ ምናልባት የምለው ነገር ካለኝ ያኔ እንገናኛለን፡፡ አሁን ከቀረበው ግምገማ ተነሥቸ ግን ከማልስማማበት ጉዳይ አንዱ “ለኢትዮጵያዊያን ሠማዕታት በቂ ትኩረት አልተሰጠም” የሚለው ትክክል አይመስለኝም ከስንክሳር አንጻር ምን ያህል ግልጽ ዳታ (አኃዛዊ መረጃ) እንደቀረበበትና እያሉ ተዘነጉ የተባሉ አባቶችን አሁንም ተጨባጭ አኃዛዊ መረጃ ጠቅሷል አልጠቀሰም የሚለውን ባላይም፡፡ በሌላ በኩል እንዲያውም ቤተክርስቲያኗ በሌሎች እኅት አብያተክርስቲያናት ዘንድ ትታማ የነበረው የእኛ እውቅና ሳይኖራቸው በራሷ ፈቃድ የራሷን አባቶች የቅድስናና “በእደ እግዚአብሔር የተሾሙ የተቀቡ ጳጳሳት” እያለች ለበርካታ አባቶች ዕውቅና ትሰጣለች ትሠይማለችም እየተባለች እንደምትታማ መጠቆም እወዳለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment