በ ፀጋው መላኩ

ዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት የሚኮንን መፅሐፍ ባለፈው ሐሙስ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለምርቃት በቅቷል። መፅሐፉ ዶክተር ዴቪድ ሆሌ በተባሉ ፀሐፊ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የታተመ ሲሆን “JUSTICE DENIED The Reality of the International Criminal Court.” ወይም በአማርኛው “የተነፈገ ፍትህ፤ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እውነታዎች” የሚል ይዘት ያለው ነው። መፅሐፉ በ609 ገፆች የተዋቀረ ሲሆን ዋነኛ ጭብጡ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICC) የአውሮፓውያን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ መሳሪያ በመሆን በሌላው የዓለም ክፍል በተለይም በአፍሪካ ኢፍትሃዊነትን እያራመደ መሆኑን ለመግለፅ ነው። ፀሐፊው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አውሮፓውያን በአፍሪካ የማይፈልጉትን መሪ ለማስወገድ የሚጠቀሙበት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያቸው መሆኑን በመጥቀስ ሀገራቱ ፍርድ ቤቱን በከፍተኛ ገንዘብ የሚያግዙ በመሆናቸው የፈለጉትንም ዓላማ በፍትህ ስም የሚያስፈፅሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ፀሐፊው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ስሙ እንደሚያመለክተው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አለመሆኑንም በዕለቱ አብራርተዋል። ፍርድ ቤቱን ለመቋቋም የተፈረመው ስምምነት የሮም ስምምነት (Rome Statute) በመባል የሚታወቅ ሲሆን እስከ 2013 ድረስ 121 ሀገራት የፍርድ ቤቱ አባል ሀገራት መሆናቸውን ገልፀዋል። 31 ተጨማሪ ሀገራት ስምምነቱን ቢፈርሙም ፊርማቸውን ያላፀደቁ መሆናቸውን አመልክተዋል። ፀሐፊው ፍርድ ቤቱ እንደስሙ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አይደለም ሲሉ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን በመስቀመጥ ነው። በአንድ መልኩ ኃያላን የተባሉ እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና ሩስያን የመሰሉ ሀገራት የፍርድ ቤቱ አባል ሀገራት ያለመሆናቸውን በመግለፅ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ከህዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይም በፍርድ ቤቱ የሥልጣን ጥላ ስር ያለው የዓለም ህዝብ ቁጥር ከአጠቃላይ የዓለማችን ህዝብ አንፃር ሲታይ ከአንድ ሶስተኛ በታች መሆኑን በመስቀመጥ ነው።
በዓለማችን ከፍተኛ የህዝብ ቀጥርን ከያዙት አስር ሀገራት ውስጥ ስድስቱ የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሀገራት አለመሆናቸውን ፀሐፊው በሃሳባቸው ማጠናከሪያነት ያስቀምጣሉ። እንደምሳሌ ያህልም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብን የያዘችው ቻይና፣ 1 ቢሊዮን ህዝብ ያላት ህንድ፣ 230 ሚሊዮን ህዝብን ያቀፈቸው ኢንዶኔዥያ እንደዚሁም 150 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሩስያ እንደዚሁም ጃፓንም 125 ሚሊዮን ህዝብን የያዘች ሀገር ብትሆንም፤ ሀገራቱ ግን የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሀገራት አለመሆናቸውን በመግለፅ መከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ዶክተር ሆሌ በሌላ መልኩ ፍርድ ቤቱ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና የአህጉሪቱን መሪዎች እንደዚሁም የአማፅያን አመራሮችን በመክሰስ ግጭቶች እንዲባባስ ያደረገ መሆኑን ነው የገለፁት። እንደምሳሌ ያህልም የኡጋንዳን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን እንደዚሁም የሱዳን ዳርፉርን ጉዳይ አንስተዋል። አውሮፓውያኑ በሀገራቸው ከፍትህ ይልቅ ሰላምን ያስቀደማሉ ያሉት ዶክተር ዴቪድ ሆሌ፤ በአፍሪካ ግን ከሰላም ይልቅ ፍትህ መቅደም አለበት የሚል አቋም ያላቸው መሆኑን አመልክዋል። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሰሜን አየርላንድ መካከል ተከስቶ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስታውሳሉ። በዚህ እርስ በእርስ ጦርነት በርካታ ሰዎች አልቀው ብዙ ንብረት ቢወድምም ለሰላም ሲባል ግን በመጨረሻ ሰዎችን በህግ የማሳደዱ ስራ ያልተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህም በዩናይትድ ኪንግደም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው መሆኑን የገለፁት ፀሐፊው፤ አውሮፓያኑ የአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ በሰላም ድርድር ሳይሆን በሕግ እንዲያልቅ ለማድረግ በመጣር በአህጉሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም ዋነኛው መሳሪያ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መሆኑን ገልፀዋል።
No comments:
Post a Comment